
አዲስ አበባ: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እና ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች በሚመለከት በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ሕዝባዊ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
በኮንፈረንሱ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር ዓይናለም ንጉሴ፣ የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ስንቄዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
ፓርቲው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ የሀገርን ኢኮኖሚ ግንባታ ማፋጠን፣ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ ያላትን ተደማጭነት ማሳደግ፣ የሕዝቦችን ሰላም እና አብሮነት ማጠናከር፣ የሕግ የበላይነትን ማስፈን እና ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ የሚሉት መኾናቸውን የገቢዎች ሚኒስትሯ ዓይናለም ንጉሴ ገልጸዋል።
ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እና በጥራት በመገንባት፣ ጠንካራ እና ገለልተኛ የፍትሕ ተቋማትን መገንባት፣ ሠላምን ማጽናት እና ግጭቶችን መፍታት፣ የታጠቁ ኃይሎች የመንግሥትን የሠላም ጥሪ ተቀብለው እንዲገቡ ማድረግ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ሚኒስትሯ አንስተዋል።
ፓርቲው በቀጣይም የሀገርን ብልጽግና እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ አስር የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
በቀጣይ የሀገርን ኢኮኖሚ መገንባት፣ ሠላምን የማጽናት፣ ግጭቶችን ማስቀረት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዓውድ መፍጠር፣ የሕግ አሥከባሪ አካላትን መገንባት፣ ጠንካራ ነጻ እና ገለልተኛ የፍትሕ ሥርዓት መገንባት ፓርቲው አበክሮ የሚሠራባቸው ተግባራት እንደኾኑም የገቢዎች ሚኒስትሯ ዓይናለም ንጉሴ ገልጸዋል።
ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን መገንባት፣ ጠንካራ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ መገንባት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እና ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ ማድረግ የፓርቲው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ባለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር በግብርና፣ በጤና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ እና በሥራ ዕድል ፈጠራ የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል መንግሥት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ: ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!