
ጎንደር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ለሦስት ወረዳዎች እና ለሦስት የጤና ተቋማት የተሽከርካሪ ድጋፍ አድርጓል።
ዞኑ ከክልሉ ያገኘውን ስድስት አምቡላንሶች እና 2 ሪቮ ተሽከርካሪዎችን ነው ለሦስት ወረዳዎች እና ለሦስት ሆስፒታሎች ድጋፍ ያደረገው።
ምሥራቅ በለሳ፣ ኪንፋዝ በገላ እና ማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳዎች የአምቡላንስ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲኾኑ ድጋፍ የተደረገላቸው የዞኑ ሆስፒታሎች ደግሞ ማክሰኝት፣ ጎሃላ እና ሻውራ ሆስፒታሎች ናቸው።
ሪቮው መኪና ደግሞ ለዞኑ ጤና መምሪያ እና ለማክሰኝት ሆስፒታል አገልግሎት የሚውሉ መኾናቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ገበያው አሻግሬ አስረድተዋል።
ተሽከርካሪዎቹ ወረዳዎች ካላቸው የሆስፒታል ተደራሽነት እና ካለባቸው ችግር በመነሳት መደልደሉን ኀላፊው ጠቅሰዋል።
የስምንቱ ተሽከርካሪዎች ዋጋም 90 ሚሊዮን ብር እንደኾነ ነው የገለጹት።
በርክክብ ሂደቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ የክልሉ ጤና ቢሮ የዞኑን የአምቡላንስ ችግር ተረድቶ ላደረገው ድጋፍ አመሥግነዋል።
ተሽከርካሪዎችን የተረከቡ ወረዳዎች እና ሆስፒታሎች ለታለመለት ዓላማ ብቻ መኪናዎችን እንዲጠቀሙ አሥተዳዳሪው አሳስበዋል።
ተሽከርካሪዎቹን ለጤና ተቋማት ማዳረስ የእናቶችን እና የሕጻናትን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም የጤና ሥርዓቱን ለማዘመን እንደሚያግዝ ተነስቷል።
አምቡላሶችን የተረከቡት የማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳ አሥተዳዳሪ ደስታው አለባቸው እና የማክሰኝት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ መንግሥቱ በሬ ለተደረገው ድጋፍ አመሥግነዋል።
አስተያየት ሰጭወቹ ተሽከርካሪዎችን በአግባቡ በመጠቀም ለታለመለት ዓላማ እንደሚያውሉ ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ:- አገኘሁ አበባው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!