አብን አዲስ የሽግግር መንግሥት ለወቅቱ አገራዊ ሁኔታ መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌለው ገለጸ።

229

ምርጫው እስኪካሄድ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መቆየትና የሽግግር ሂደቱን መምራት ለሕዝብ እና ለአገር ሰላምና ደኅንነት በአንጻራዊነት የተሻለ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ገልጿል።

የአብን ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 26 እና 27 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ አውዶችን በመገምገም፣ የአማራ ሕዝብን ወቅታዊ አቋምና ዘላቂ ጥቅሞችን፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኃይሎች ፍላጎቶችን እና የቀረቡ አማራጮችን በመመርመር መግለጫ ማውጣቱን አስታውቋል።

ንቅናቄው በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተቋማት ላቀረቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ክብር ያለው መሆኑን በማሳወቅ ለወቅቱ አገራዊ ሁኔታ አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌለው ገልጿል።

ከዚህ ይልቅ የተወሰነ የሽግግር ጊዜ መፍጠር የተሻለ አማራጭ መሆኑን ያሳወቀው አብን ይህም “የአገራችን እጣፋንታ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲቆም ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ነባራዊ ውጥረቶችና ክፍተቶች እንዲረግቡና የጥሞናና ውይይት መንፈስ እንዲሰፍን ያስችላል” ብሏል፡፡

የሽግግር ጊዜ ያላሰለሰ ሕዝባዊ ውይይት፣ ልሂቃዊ ምክክርና ድርድር እንዲደረግና ሊያሰራ የሚችል ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር እድል ይሰጣል የሚለውም ሌላው ምክንያት ነው ብሏል ንቅናቄው።

Previous articleየአገው ብሔራዊ ሸንጎ ዓላማውን እየሳተ በመሆኑ ድርጅቱን መልቀቃቸውን ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አዲሱ መኮንን አስታወቁ።
Next articleየአገው ምሁራን ማኅበር ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ አደረገ፡፡