
ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ኮንፈረንስ በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ሕዝባዊ ኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር) በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የቀረቡ ውሳኔዎችን እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ለትውልድ እንድትተላለፍ እና ጠንካራ የኾነች ሀገር እንድትኖረን ከተፈለገ፣ ጠንካራ ፓርቲ፣ ጠንካራ መንግሥት፣ ጠንካራ እና ሕዝብን ዝቅ ብለው የሚያገለግሉ መሪዎችን መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ሕዝብን የሚያገለግሉ መሪዎችን ማበረታታት፣ በሁለት ቢላ የሚበሉትን እና ሕዝብን የሚያማርሩትን ደግሞ ማጽዳት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለሕዝብ የሚጨነቅ መሪ መፍጠር የቀጣይ አቅጣጫ ነው ብለዋል። ከመለያየት በመውጣት አንድነት እና ኅብረ ብሔራዊነትን ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል። የአንድነት፣ የትስስር እና የኅብረት መንፈስ በኢትዮጵያ ማጠናከር እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት።
ኅብረት እና አንድነት የሚያጠናክር ሥራ እንሠራለን ብለዋል። “አንድነት፣ ኅብረት እና ፍቅር ለሁላችን ይበጀናል” ነው ያሉት። ኢትዮጵያን በአንድነት የሚያሰባስብ ሥራ እንሠራለን ብለዋል። እንሰባሰባለን እንጂ አንነጣጠለም ነው ያሉት።
ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሰፍን እንሠራለንም ብለዋል። ሰላምን ለማምጣት እና ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ተዘዋውረው እንዲሠሩ እንደሚሠራም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሰላም እንዲመጣ ማንኛውንም የሰላም አማራጭ እንከተላለን ነው ያሉት።
ሁሉም ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ይደረጋል፣ የሰላም ጥሪ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የሕዝብ ሰቆቃ እንዳይኖር በአንድ እጅ ሰላም በአንድ እጅ ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ውጤታማ የፍትሕ ሥርዓት እንዲገነባ በትኩረት እንዲሠራ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል።
ፍትሕ በእኩልነት እንዲተገበር ይሠራል ነው ያሉት። ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ እንዲያምኑ እና እውነተኛ ፍትሕ እንዲያገኝ ይደረጋል ብለዋል። ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት እና እንዲያድግ የሚያደርጉ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል። የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የሁሉም ዋስትና እንድትኾን ኢትዮጵያዊነትን እንገነባለን ነው ያሉት። መነጣጠል አላዋጣንም ወደፊትም አያዋጣንም፣ በሚቀጥሉት ዓመታት በሚያዋጣን ኢትዮጵያዊነት ላይ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል። በሁሉም ነገር የተሳካላት ሀገር እንድትኾን እና የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንገነባለን ብለዋል። ገቢ የማሳደግ እና የከተሞችን ልማት የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። የልማት አርበኛ ትውልድ የመገንባት ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ጥላቻን ሳይኾን ፍቅርን፣ መጠራጠርን ሳይኾን መተማመንን እንገነባለን ነው ያሉት። ጉዳያችን የኢትዮጵያን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ እና ማበልጸግ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያን ዘላቂ እና ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች እንደሚሠሩም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። የአገልግሎት አሰጣጥ የተሰካ እና የተሳለጠ እንዲኾን በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል። መሪዎች እና ባለሙያዎች ሕዝብን ዝቅ ብለው እንዲያገለግሉ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ዜጎች በአገልግሎት የሚረኩ እና የሚደሰቱ እንጂ የሚማረሩ እንዳይኾኑ ይሠራል ነው ያሉት። ሀሰተኛ የሚዲያ አጀንዳዎችን እንታገላለን፣ ሚዲያውን ለሀገር ግንባታ እንጠቀማለን ነው ያሉት። ከድህነት የወጣች ሀገርን ለልጆቻችን እናስረክባለንም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!