
ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የስያሜ እና የንግድ ምልክት የማስተዋወቅ መርኃ ግብር አካሂዷል።
በትውውቅ መርኃ ግብሩ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የቀድሞው የአማራ ሕንጻ ሥራዎች ድርጅት የአደረጃጀት፣ የስያሜ እና የመለያ ለውጥ ማደረጉን ስናበስር በደስታ ነው ብለዋል። የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ለኢኮኖሚው ዘርፍ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል።
የሕዝባችን የመሠረተ ልማት እና የመልማት ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንደ ዘመን ኮንስትራክሽን ያሉ ተቋማት ድርሻቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲነቃቃ የአሁኑ የስያሜ ለውጥ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንደ ሀገር እያደገ መጥቷል ያሉት ኀላፊው የአሁኑ ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ከተቋቋመበት 1998 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ግን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም ነው ያሉት።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የበለጠ እንዲያንሠራራ በርካታ ማነቆዎች እንደነበሩም አስታውሰዋል። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ተግባራት ሲሠሩ ቆይተዋል። ቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የክልላችን መንግሥት የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ አለው ያሉት ዶክተር አሕመዲን ከዚያ የተቀዳም የአስር ዓመት የስትራቴጅክ ዕቅድ ታቅዶ በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከተያዘው የስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ ደግሞ የኮንስትራክሽን ዘርፍን የማዘመን ተግባር ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል።
ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንን የበለጠ ለማሳደግ በቀጣይ አምስት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ እናተኩራለን ብለዋል። የአሠራር ሥርዓቶችን ማዘመን፣ የሰው ኀይል ዘመኑን የዋጀ እንዲኾን ማድረግ፣ ቴክኖሎጅን ማዘመን እና ማስፋት፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ትብብሮችን ማጠናከር እንዲሁም የታቀዱ ተግባራት ግባቸውን እንዲመቱ ጥብቅ ክትትል ማድረግ ዋና ዋና ነጥቦች ይኾናሉ ነው ያሉት።
የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ፕሮጀክት እዚህ እንዲደርስ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!