ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የስም እና የንግድ ምልክት ለውጥን ይፋ አደረገ።

42

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፓሬሽን አዲስ የስም እና የንግድ ምልክት ይፋ አድርጓል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ታደሰ ግርማ ይህ እርምጃ የድርጅቱን ዕድገት እና ለውጥ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰው አሁን ወደ ቤቶች ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ዘርፍ አስፋፍቷል ነው ያሉት።

ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በክልሉ መንግሥት የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶችን በጊዜ፣ በጥራት እና በመጠን በማጠናቀቅ ለውጥ እያመጣ መኾኑን ነው አቶ ታደሰ የተናገሩት።

ኮርፖሬሽኑ የግንባታ ግብዓት ችግርን ለመቅረፍ እና የገበያ መረጋጋትን ለማምጣት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነውም ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እራሱን እያዘመነ እንደኾነ ገልጸዋል። በኮርፓሬሽኑ የተከናወኑ ሥራዎችን ዋና ሥራ አስኪያጁ ሲገልጹ በ964 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ካፒታል ዘመን ተሻጋሪ ሕንፃዎችን ገንብቷል ብለዋል።

ከክልሉ ውጭ በ12 ከተሞች ከ884 በላይ ሕንጻዎችን እና ከ20 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች አስረክቧል ብለዋል።

32 ትላልቅ የአሥተዳደር ሕንጻዎችን፣ 24 የዩኒቨርሲቲ ሕንጻዎችን፣ 31 የኢንዱስትሪ እና የገጠር ሽግግር ማዕከላትን፣ 5 የባሕል ማዕከል፣ 3 የትራፊክ እና የአውቶቡስ መናኸሪያ እና 84 ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ገንብቷል ብለዋል።

ከክልሉ ውጭ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 306 የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ገንብቷል ነው ያሉት። በመንገድ ሥራ ዘርፍም 95 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ ሠርቷል ነው ያሉት።

ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ እያደረገ ነው። ይህም የመዋቅር እና የደረጃ፣ የአሠራር እና ማዕቀፍ፣ የንግድ ምልክት እና ስያሜ፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ እና የሥራ ቦታ ማሻሻያዎችን ያካትታል ነው ያሉት።

የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አዲሱ ስያሜ እና የንግድ ምልክት ይፋ መደረጉ ለድርጅቱ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትም ይጠበቃል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች ዳር እንዲደርሱ ሕዝቡ ርብርብ እንዲያደርግ ተጠየቀ።
Next article“የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ለኢኮኖሚው ዘርፍ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)