
ጎንደር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ዉሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ዙሪያ ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በዉይይቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ.ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘውን ጨምሮ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ጥሪ የተደረገላቸዉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በተፈጠረው የሰላም እጦት በጎንደር ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ አሳድሮ መቆየቱን አንስተው መንግሥት በከተማዋ እያካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት ተስፋ ሰጭ የልማት ጅምሮች መታየታቸውን አስታውቀዋል።
መንግሥት የጎንደር ከተማን ለማልማት እያደረገ ላለው ጥረትም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ምሥጋና አቅርበዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ.ር) በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች ዳር እንዲደርሱ መንግሥት እና ሕዝብ በኅብረት ለውሳኔዎቹ መሳካት ርብርብ እንዲያደርጉ ያለመ ምክክር መኾኑን አንስተዋል።
የውይይት መድረኩ በጎንደር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል፣ የሕዝቡን ቀሪ የመልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል መኾኑን ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በጎንደር ከተማ የተሠሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን መመልከታቸውን ገልጸው መሰል የልማት ሥራዎችን ለማስፋፋት እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማጠናከር ውይይቱ አስፈላጊ መኾኑን አስረድተዋል።
ዘጋቢ:-አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን