
ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ኮንፈረንስ በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ሕዝባዊ ኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።
በሕዝባዊ ኮንፈረንሱ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ለውጦች ተካሂደዋል፣ የተካሄዱት ለውጦች ግን የሕዝብን ጥያቄ በሙሉ መመለስ የቻሉ አልነበሩም ነው ያሉት።
የተካሄዱት ለውጦች የሕዝብን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ የመለሱ ባለመኾናቸው ሕዝብ ለውጥን ሲሻ ኖሯል ነው ያሉት። ብልጽግና ፓርቲም የለውጥ ፍላጎት የወለደው እና ጠንካራ እና ባለ ታላቅ ራዕይ ነው ብለዋል። ብልጽግና ፓርቲ የጋራ ሀገርን የመገንባት ሥራ የሚሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በአንድነት የመልማት እና የመበልጸግ ራዕይን ይዞ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ሥራዎችን መሥራቱንም ገልጸዋል። የብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ ቁርሾ የፈጠሩ ችግሮችን ለማከም፣ በአንድነት እና በኅብረት የተገነባች፣ የተመቸች ሀገር ለመገንባት አልሞ የተነሳ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ባለፉት ጊዜያት በፈተና መቆየቱን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላሙም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ላደረገው ሁሉ ምስጋና አቅርባለሁ ነው ያሉት። ለአማራ ክልል ሰላም የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይል ክቡር መስዋዕትነት ከፍሏል ነው ያሉት። ላደረገው ሁሉም ምስጋና እና ክብር አለን ነው ያሉት። አሁን ሰላማችን እየተመለሰ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሕዝባችን ተጎሳቁሏል ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ የሚመለሰው በመገዳደል ሳይኾን በአንድነት እና በፍቅር መኾኑን ነው ያነሱት። “አንድ እንሁን፣ የግጭትን ምዕራፍ እንዝጋ” ብለዋል በመልዕክታቸው።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ዓላማ ሰላምን በኢትዮጵያ ማንገስ እና ችግርን በውይይት መፍታት ነው ብለዋል። ሰላማችንን እናጽና፣ ልማታችንን እናስቀጥል ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ኾኖ ኢትዮጵያን ያስቀጥላል። ይህ ደግሞ ከአባቶቻችን የተረከብነው አደራ እና ቃል ነው ብለዋል። የተጀመረው ሰላም እንዲጸና እና ልማት እንዲፋጠን በጋራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን