“የሰላም ተምሳሌት የኾነች ባሕር ዳርን ስላሳያችሁን እናመሰግናችኋለን” ርእሰ መሥተዳደር ጥላሁን ከበደ

23

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ሕዝባዊ ኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።

በሕዝባዊ ኮንፈረንሱ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ባሕር ዳርን ከውጭ ስንሰማ ተስፋ የሌላት፣ የመከራ፣ የሰቆቃ ከተማ እንደኾነች ነበር። መጥተን ስናያት ግን ልማት የሚፋጠንባት፣ የሰላም ተምሳሌት፣ እውነተኛ የጣና ፈርጥ ምድራዊ ገነት የኾነች ናት ብለዋል። አሁን ላይ በቀን ብቻ ሳይኾን በማታ የሚሠራባት ከተማ ማየታቸውንም ተናግረዋል።

“የሰላም ተምሳሌት የኾነች ባሕር ዳርን ስላሳያችሁን እናመሰግናችኋለን” ነው ያሉት። የአማራ ክልል ሕዝብ ኩሩ፣ ኢትዮጵያን ለዘመናት አጽንቶ ያቆመ ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል። ሀገር ያቆመ ሕዝብ ውስጣዊ ችግሮችን መፍታት እንዳለበትም አመላክተዋል።

የገጠመውን ጊዜያዊ ችግር መፍታት እና በቀደመው ክብር ልክ መቆም ይገባዋል ነው ያሉት። ግጭት ለአማራ ሕዝብ ክብር እና ታሪክ እንደማይመጥንም አንስተዋል። መሪዎቻችሁን አግዟቸው፣ እንወያይ፣ ችግሮቻችን በሰላም በውይይት እንፍታ ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ፈተናዎችን ወደ እድል የሚቀይር መኾኑን ገልጸዋል። በብልጽግና ፓርቲ የተወሰኑ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን ከሕዝብ ጋር እንመክራለን፣ አብረን እንፈጽማቸዋለን ነው ያሉት። በጋራ ኾነን ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ብለዋል።

የተሻለ ሥራ ለመሥራት ትልቁ አቅም ሕዝብ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ ሕዝብን ከያዝን የምንፈልገውን ስኬት በአጭር ጊዜ እናሳካለን ነው ያሉት። ሰላምን እና ለውጥን የማይፈልጉ አካላት አሁንም ይፈትኑናል፣ ነገር ግን ፈተናውን በአንድነት እናልፈዋለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአንድነት እና በነጻነት መኾኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከሌሎች ተለይታ የድል ቀን የምታከብር ብቸኛ ሀገር ናት ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ በውጭ ወረራ ላይ እንደዘመትነው ሁሉ በድህነት ላይ ዘምተን ድህነትን ድል መምታት አለብን ብለዋል።

የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ቃላችንንም በተግባር አሳይተን የሚጨበጥ እድገት ማምጣት አለብን ብለዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ የሚያኮራ መኾኑንም ተናግረዋል። ባሕር ዳርን ተናፋቂ እና የተመቸች አድርጋችኋታል ክብር ይገባችኋል ነው ያሉት። በቀን መንቀሳቀስ አይቻልባትም እየተባለ በሚነገርባት ከተማ እኛ ግን በምሽት ተንቀሳቅሰን ሰላም መኾኗን አረጋግጠናል ብለዋል።

ሀሜተኛው ሀሜቱን ይቀጥል እናንተ ግን ሥራችሁን ቀጥሉ ብለዋቸዋል። ከተማዋ ከዚህ የበለጠ የኢንዱስትሪ እና ዓለም አቀፍ ከተማ እንድትኾን በጽናት ሥሩ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሕዝባዊ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ተጀመረ።
Next article“አንድ እንሁን፣ የግጭትን ምዕራፍ እንዝጋ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው