
የትኛውም አካል የአገውን ሕዝብ የፖለቲካ አጀንዳው ማስፈጸሚያ ሊያደርገው እንደማይችል የሸንጎው ምክትል ሊቀ-መንበር ተናግረዋል።
ምርጫው እንዲራዘም የተወሰነው ውሳኔ ወቅቱን የጠበቀና አማራጭ የሌለው ስለመሆኑም አቶ አዲሱ ተናግረዋል።
የሸንጎው ምክትል ሊቀ-መንበር የነበሩት አቶ አዲሱ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት “ሸንጎው የወከለውን ሕዝብ መብትና ጥቅም ከማስከበር ይልቅ የህወሃት አጀንዳ ማስፈጸሚያ ሆኗል”። ሸንጎው የሕዝቡን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ እኩል የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ እንደነበረም አስታውሰዋል።
ይሁንና በተለይ ”የሸንጎው ሊቀ-መንበር ከህወሃት ጋር ባላቸው ልዩ ቅርበት የወከሉትን የአገው ሕዝብ ረስተው በሕዝቡ ስም የህወሃት አጀንዳ አስፈጻሚ ሆነዋል” ነው ያሉት።
ይህን በመቃወምም እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የሸንጎው ሥራ አስፈጻሚ አባላት በተደጋጋሚ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥያቄ ቢያቀርቡም መፍትሄ ባለመምጣቱ ሸንጎውን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያታቸው ”የአገው ሕዝብ የማንም አጀንዳ አስፈጻሚ መሆን የለበትም የሚል ነው”።
አቶ አዲሱ ”ሸንጎው የወከለውን ሕዝብ መብትና ጥቅም እንዲያስጠብቅ ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ትግላችንን ግን አናቋርጥም” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም የወሰነው ውሳኔ ወቅታዊና አማራጭ የሌለው መሆኑን አቶ አዲሱ ነናግረዋል። አገሪቱ በአሁኑ ወቅት የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ከግብጽ ጋር በሌላ መልኩ ደግሞ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ትንቅንቅ ውስጥ መግባቷን በማስታወስም ይህን ችግር ለመፍታት ከፖለቲካ ጨዋታ በመውጣት በአገር ስሜት መተባበርና ችግሩን በጋራ መወጣት ላይ ከማተኮር ይልቅ የራስን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ መሯሯጥ ኢ-ሰብዓዊነት ነው ብለዋል።
የአገው ብሔራዊ ሸንጎ የአገውን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር በሚል ጥር 5 ቀን 2011 ዓ .ም መመስረቱ ይታወቃል።