
ባሕር ዳር: የካቲት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር መቶ በመቶ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን የከተማ አሥተዳደሩ ገልጿል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ባወጣው አቅጣጫ መሠረት ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ በደሴ ከተማ ትምህርት መምሪያ የትምህርት ልማት ስትራቴጅክ ትንተና ዕቅድ ዝግጅት እና ሃብት ማፈላለግ ቡድን መሪ ወንድወሰን አረጋ ነግረውናል።
በአሁኑ ወቅት አንደኛው ወሰነ ትምህርት ተጠናቅቆ ሁለተኛው ወሰነ ትምህርት እየተካሄደ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
አቶ ወንደሰን አረጋ በደሴ ከተማ አሥተዳደር ስር ባሉ ትምህርት ቤቶች 66 ሺህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ተማሪዎች በአጸደ ሕጻናት፣ በአንደኛ ደረጃ፣ በሁለተኛ ደረጃ እና መሠናዶ እንዲሁም በርቀት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በተጨማሪም 55 አጸደ ሕጻናት፣ 53 አንደኛ ደረጃ፣ 14 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማሩን ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ነው የነገሩን።
በአካባቢው ያለው ሰላም ለመማር ማስተማሩ ሥራ አግዟል ያሉት ቡድን መሪው ትምህርት ለትውልድ በሚል በተሠራው ንቅናቄ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ ተችሏል ነው ያሉት።
ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ የትምህርት ቁሳቁስ የማሠባሠብ ሥራ ስለመሠራቱም ነው የጠቆሙት።
ከኢኮኖሚ አኳያ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ በከተማ አሥተዳደሩ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ እና በኅብረተሰቡ እገዛ ተማሪዎችን መመገብ ስለመቻሉም አስገንዝበዋል።
የአካባቢው ሰላም ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል የሚሉት ቡድን መሪው “የደሴ ሕዝብ በትምህርት በኩል ሞዴል መኾኑን አስመስክሯል” ነው ያሉት።
ቡድን መሪው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!