
አዲስ አበባ: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች ጋር አራተኛውን ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ኮንፈረንስ አካሂዷል። ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው ከዘጠነኛው ኢትዮ ሄልዝ ኤግዚቢሽን ጋር በመተባበር ነው። በኤግዚብሽኑም የግል እና የመንግሥት መድኃኒት አቅራቢዎች ተሳትፈዋል።
ኮንፈረንሱ እና ኤግዚቢሽኑ “ለጋራ ርዕይ ጠንካራ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፋዊ ጥምረት መገንባት” በሚል መሪ ሃሳብ የቀረበ ነው። በኮንፈረንሱ ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች እየጨመሩ ነው ብለዋል። ለበሽታዎች መፍትሄ አምጭ መድኃኒቶችን ለማምረት እና ለፈላጊዎች ለማቅረብ ካለፈው በተሻለ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በኮንፈረንሱ የተሳተፉ አስመጭ እና አምራቾች በቀጣይ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የጋራ የኾነ ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል። የኮንፈረንሱ እና ኤግዚብሽኑ መዘጋጀት ለሀገር ጠቃሚ የኾኑ መድኃኒቶችን የሚያመርቱ እና የሚያስመጡ ድርጅቶችን ለማበረታታት ይጠቅማል ተብሏል። በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱርቃድር ገልገሎ ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ላለፉት 77 ዓመታት መሠረታዊ የኾኑ ሕይዎት አድን መድኃኒቶችን ለሕዝብ ሲያቀርብ የቆየ ነውም ተብሏል። የኢትዮጵያ መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ ኢትዮጵያ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት የተሻለ ምቹ የኾነ አየር ንብረት ቢኖራትም በቂ የኾነ መድኃኒት ማምረት እና ማቅረብ አለመቻሏን አንስተዋል።
ዶክተር ዳንኤል በቀጣይም ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከውጭ የሚመጡ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን