“በሦስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄ ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መመለስ ተችሏል” የምዕራብ ጎጃም ዞን

26

ባሕር ዳር: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ በተጀመረው ሦስተኛ ዙር የምዝገባ ዘመቻ 5 ሺህ 610 ተማሪዎች መመዝገባቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ። በአማራ ክልል 4 ሚሊዮን የሚደርሱ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታቸው ተደናቅፈዋል። ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ለትምህርት ዕድሜ የደረሱ ሕጻናትም በ2017 ዓ.ም ትምህርት ቤት አልተገኙም። ይህም የኾነው በክልሉ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ነው።

በተለይም የምዕራብ ጎጃም ዞን በ2016 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ የመማር ማስተማር ሥራ ካልተከናወነባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በ2017 የትምህርት ዘመን 396 ሺህ 547 ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሳሉ ተብለው የሚጠበቁ ቢኾንም እስካሁን ድረስ 28 ሺህ 931 ተማሪዎች ብቻ ናቸው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት።

ይሁን እንጂ ትምህርት የተቋረጠባቸውን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲኾን ከነዚህም መካከል አንዱ የሦስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ዘመቻ ይጠቀሳል። የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ መኩሪያው ገረመው እንደገለጹት ከየካቲት 3 እስከ 13/2017 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው ምዝገባ 5 ሺህ 610 ተማሪዎች ተመዝግበዋል። መምሪያው እነዚህን ተማሪዎች ለማብቃት የትርፍ ሰዓት ትምህርት ለመስጠት እና አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑንም አቶ መኩሪያው ገልጸዋል።

ዘጋቢ :- ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ2 ሺህ 900 በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መመለሳቸውን የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
Next articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ለማካሄድ ባሕር ዳር ከተማ ገቡ።