
ባሕር ዳር: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ እያካሄደ መኾኑን የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። በአማራ ክልል ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ እና ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ውጭ እንዲኾኑ አድርጓል። በግጭት ምክንያት ትምህርት ቤቶች ከተዘጉባቸው አካባቢዎች መካከል የምስራቅ ጎጃም ዞን ተጠቃሽ ነው።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ በ2017 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል 713 ሺህ 610 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር አቅዶ እንደነበር የመምሪያው ምክትል ኀላፊ ደመላሽ ታደሠ ለአሚኮ ተናግረዋል። ክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ628 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ነው አቶ ደመላሽ የተናገሩት።
ከትምህርት ውጭ የኾኑትን ተማሪዎች ለመመለስ በተከታታይ ሢሠራ ቆይቷል ነው ያሉት። በአንደኛው እና በሁለተኛው ዙር በምዝገባ ንቅናቄ ተማሪዎች ተመዝግበዋል፤ ይህም ኾኖ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደኸኑ ነው የገለጹት። ያቋረጡ ተማሪዎች ለሥነ ልቦና ችግር እየተጋለጡ ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው ወላጆች ሴት ተማሪ ልጆቻቸውን ትምህርት ከተቋረጠ በሚል ሰበብ ያለ ዕድሜያቸው እየዳሯቸው ይገኛሉ ነው ያሉት።
በሦስተኛው ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄ ውጤት ለማምጣት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ የትምህርት ባለድርሻዎችን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን፣ የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን በማወያዬት መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተጨባጭ ሥራ መገባቱንም ነው አቶ ደመላሽ የተናገሩት። ሦስተኛውን ዙር የተማሪዎች ምዝገባ በንቅናቄ እና ርብርብ በመሥራት ተዘግተው የነበሩ ሦስት የአጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋልም ብለዋል።
አምስት የአንደኛ ደረጃ እና ሦስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ማስተማር መጀመራቸውንም ተናግረዋል። “በሦስተኛው ዙር የተማሪዎች ምዝገባም 2 ሺህ 951 ተማሪዎች ተመዝግበው በመማር ላይ እንደሚገኙ” የትምህርት መምሪያው ምክትል ኀላፊ ገልጸዋል።
መማር ማስተማሩን ለማስቀጠል አሁንም የጸጥታው ችግር ፈተና እንደኾነ ቀጥሏል ያሉት አቶ ደመላሽ ወላጆች ሴት ተማሪ ልጆቻቸውን “ትምህርት ከተቋረጠ” በሚል ሰበብ ያለ ዕድሜያቸው እየዳሯቸው ይገኛልና የሚመለከተው ሁሉ ጉዳዩን ችላ ሊለው አይገባም ብለዋል።
ማንኛውም አካል ትምህርት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነጻ መኾኑን በመገንዘብ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት። የነገዋ ኢትዮጵያ ጸንታ የምትቀጥለው የዛሬ ሕጻናት በአግባቡ ትምህርታቸው ሲቀጥሉ እንደኾነም ተገልጿል።
ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!