
ሰቆጣ: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ባለፈው ክረምት በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች የመድኃኒት እና የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፉን ያስረከቡት የወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የጥናት ቡድኑ መሪ ድንበሩ በሬ በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በተገኘ ድጋፍ 50 ኩንታል የምግብ እህል እና ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተገኘ ከ68 ዓይነት በላይ የመድኃኒት ድጋፍ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
1 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ወጭ እንደተደረገበት ያወሱት መምህር ድንበሩ በቀጣይም በጥናት ላይ የተመረኮዘ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት። ድጋፉን የተረከቡት የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና ምክትል ከንቲባ ሙሉ ሽመልስ የተደረገው የመድኃኒት ድጋፍ ለተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል እና ለአቡነ በርናባስ መታሰቢያ ጤና ጣቢያ የሚውል ይኾናል ብለዋል።
50 ኩንታል የበቆሎው ድጋፍ ደግሞ ከ330 በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የወር ቀለብ እንደሚኾን ጠቅሰዋል። በዋግ ኽምራ ባለፈው ክረምት በተፈጠረው የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከ243 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተናገሩት ደግሞ የመንገድ መምሪያ ኀላፊው ጸጋው እሸቴ ናቸው።
በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ባለፈው ዓመት በነበረው የሰሃላ ሰየምት ድርቅም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የእህል ድጋፍ እንዳደረጉ አቶ ጸጋው አሰታውሰዋል። ዛሬም የተደረገው የመድኃኒት እና የእህል ድጋፍ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለማኅበረሰቡ ያላቸውን አጋርነት ያሳዩበት ነው ብለዋል።
ለተደረገው ድጋፍ በዋግ ሕዝብ ስም አመስግነው በቀጣይም ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች፣ አጋዥ ድርጅቶች እና ግለሰቦች መሰል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ሲከፋፈሉ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙሉ አለቃ እና ወይዘሮ ፀሐይነሽ ደሴ ድጋፍ በቸገራቸው ወቅት ስለተደረገላቸው ከልብ ተደስተናል ብለዋል።
ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!