”የኮሪደር ልማትን ከተማችን ብቻ ሳይኾን የሰውንም አዕምሮ ለማልመት ተጠቅመንበታል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

32

አዲስ አበባ: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን መምሪያ ከተጠሪ ተቋማት እና አጋር አካላት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሟል። በግምገማው የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የባሕር ዳር ከተማ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማ እና መሠረተ ልማት ከነተጠሪ ተቋማቱ የባሕር ዳር ከተማን አብዛኛዎቹን ሥራዎች የሚሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ተቋሙን በልዩ ሁኔታ መምራት እና መከታተል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የኮንስትራክሽን ዘርፉን በማጠናከር የኮሪደር ልማትን ለመተግበር መሠራቱን ገልጸዋል። ሥራው የመሪዎች እና የባለሙያዎች አቅም ታይቶበታል ነው ያሉት።

ከተማዋ ከፍ ያሉ መሐንዲሶች እና መሰል ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጓት ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሀሳብ ወስደው ሕይወት ያለው፣ የሚታይ እና የሚዳሰስ የከተማ ሥራ እና ገጽታ እንዲፈጥሩ እንፈልጋለን ብለዋል። ድጋፍም እናደርጋለን ነው ያሉት። “የኮሪደር ልማትን ከተማችን ብቻ ሳይኾን የሰውንም አዕምሮ ለማልመት ተጠቅመንበታል” ብለዋል። በሕንጻ ሹም እና ሌሎች ተቋማትም የከተማዋን ጽዳት እና ውበት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሀሳቦች ወደ ተግባር መቀየራቸውን ገልጸዋል።

የመሬት ልማት ዘርፉን ለማሻሻል ሥራዎች መጀመራቸውን የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በባሕር ዳር ከተማ ሁለተኛው ሊዝ በሂደት ላይ መኾኑን አንስተዋል። ለኢንቨስትመንት የተሰጡ ቦታዎችን በማጥናት ወደ ልማት እንዲገቡ ይሠራል ነው ያሉት። ፈጣን እና አርኪ አገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በቂ አለመኾኑን እና መስተካከል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ለሰላም እጦት እየዳረገ ያለው ሕገ ወጥነት ሊስተካከል እንደሚገባም ገልጸዋል። ባሕር ዳርን ባላት ጸጋ እና በሚገባት ልክ ጽዱ እና አረንጓዴ ከተማ ለማድረግም መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከዕቅድ በላይ አስቦ በዕውቀት መሥራትን እንደሚፈልግም ጠቅሰዋል። የዓለም የከተሞች ዕድገት ተሞክሮን አውቆ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። መሪች እና ባለሙያዎች አስተሳሰባቸውን አስፍተው እና ዕውቀታቸውን አሳድገው ለከተማዋ ልማት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ :- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ ግብርና አዋጭ የሥራ ዘርፍ እየሆነ መምጣቱን የልማቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
Next articleፎረሙ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ ለሚገኙ የተቸገሩ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ።