በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ ግብርና አዋጭ የሥራ ዘርፍ እየሆነ መምጣቱን የልማቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

48

ባሕር ዳር: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ በሪሁን ማሩ የባሕር ዳር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በ3 ሄክታር መሬት ቅመማ ቅመምን ጨምሮ የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎች እና የበጋ በቆሎ የማልማት ሥራ ይሠራሉ፡፡ አቶ በሪሁን የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማትን ቀደም ብለው በትንሽ መሬት የጀመሩ መኾኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በሦስት ሄክታር መሬት ትኩስ እና ንጹህ የኾኑ እንደ ሀበሻ ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን እና የበጋ በቆሎን በማልማት ለከተማው ማኅበረሰብ እያቀረቡ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ምርት በዓመት እስከ 500 ሺህ ብር በማግኘት ኑሯቸውን በተሻለ ሁኔታ እየመሩ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የከተማ ግብርና ባለሙያዎች ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ የምክር አገልግሎት እና ድጋፍ እያደረጉላቸው መኾኑንም ነው አቶ በሪሁን የገለጹት። ወደፊት አሁን ከሚያመርቱት ምርት በተጨማሪ እና በተሻለ ሁኔታ በማምረት ለከተማው ማኅበረሰብ በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ እና ገበያውን በማረጋጋት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ነው የተናገሩት፡፡

የከተማ ግብርና በከተማ ግቢ ውስጥ በመደብ፣ በጣራ ላይ፣ በግድግዳ እና በተለያዩ ቁሳቁሶች እና ከግቢ ውጭ ባሉ ባዶ ቦታዎች መደብ በማዘጋጀት የሚሠሩ የግብርና ሥራዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሰፋ ባለ መልኩ በከተማ ውስጥ በወንዝ ዳርቻ እና በሐይቅ ዳርቻ፣ በምንጮች አካባቢ በሚገኙ ቦታዎች ላይ ማንኛውም ለምግብነት መዋል የሚችሉ እጽዋቶችን ማልማት የከተማ ግብርና ሥራዎች ናቸው፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ብቻ በበጀት ዓመቱ 635 ሄክታር መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ መልማቱን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ ሞላልኝ መንግሥቱ ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ቀይስር፣ ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም፣ የሀበሻ ጎመን፣ ዘይቱና፣ ማንጎ፣ ሀብሀብ እና መሰል አትክልት እና ፍራፍሬዎች ይለማሉ፡፡

ከዚህም 28 ሺህ 575 ኩንታል አትክልት እና ፍራፍሬ ይመረታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ምንም አይነት ገቢ የሌላቸው 1ሺህ 966 ወንዶች እና 3ሺህ 74 ሴቶች የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ለኅብረተሰቡ ትኩስ እና ጤንነቱ የተጠበቀ አትክልት እና ፍራፍሬ ከማቅረብ አኳያ ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ባለሙያው ከዚህ በፊት በነበረው ወቅታዊ ችግር መንገድ በሚዘጋበት ወቅት ቀድሞ ለገበያ በማቅረብ እና ገበያን በማረጋጋት ጉልህ ሚና እንደነበረውም ተናግረዋል፡፡

ይህንን በስፋት ለማስቀጠል እና ኅብረተሰቡ ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም የከተማ ግብርናን ልምድ አድርጎ እንዲሠራ በከተማው ባሉ ስድስት ክፍለ ከተሞች ባለሙያዎችን በመመደብ የግንዛቤ ፈጠራ እና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ በማዘጋጃ መሬት ልማት የሚያለሙ ወጣቶችን እና ተማሪዎችን በወራሚት ምርምር ማዕከል የልምድ ልውውጥ እንዲወስዱም ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በአደይ ፕሮግራም በስድስት ዙር 1 ሺህ 613 ወጣቶችን በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው ባለሙያው የተናገሩት፡፡ መምሪያው ሙሉ አቅሙን አሟጦ እንደማኅበረሰቡ ፍላጎት የማገዝ እና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ለመሥራት እጥረት እንዳለበት በማንሳት ችግሩን ለመቅረፍ ተግባሮችን እና የሚጠቀሟቸውን ግብዓቶች በዝርዝር በማስፈር ለጊዜው የሚያግዝ ጹሑፍ ለእያንዳንዱ አልሚ ተደራሽ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ የገጠር ቀበሌዎችን ጨምሮ 4 ሺህ 800 ሄክትር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለሰላም የዘረጋነውን እጅ ሳናጥፍ የልማት እና የሕግ ማስከበር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ
Next article”የኮሪደር ልማትን ከተማችን ብቻ ሳይኾን የሰውንም አዕምሮ ለማልመት ተጠቅመንበታል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው