
ባሕር ዳር: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር ክልላዊ ግምገማዊ መድረክ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ሊከናወኑ የሚገባቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በላቀ ትጋት እና ውጤት መፈጸም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሕዝቡን ሁለንተናዊ ጥቅም የሚያሟሉ ሥራዎችን ለመከወን በቅንጅት እና በትብብር መሥራት እንደሚገባ የተናገሩት ርእስ መሥተዳደሩ በሁሉም የልማት እና የመልካም አሥተዳዳደር ሥራዎች ላይ ሕዝብን ማሳተፍ እና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። ከሕዝባችን ጋር ተባብረን በመሥራታችን አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ችለናል ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ ለሰላም የዘረጋነውን እጅ ሳናጥፍ የልማት እና የሕግ ማስከበር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው የሕዝቡ ቀዳሚ ምርጫ ሰላም እና ልማት መኾኑን በየመድረኮች እና በአደባባይ ሰልፍም ጭምር ተናግሯል ነው ያሉት። እስካሁን ባሳካናቸው ድሎች ላይ በመመርኮዝ የተገኙ ስኬቶችን ማስጠበቅ እና ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት አቶ ይርጋ ሲሳይ ያጋጠሙ ውስንነቶችን በፍጥነት በመፍታት የበጀት ዓመቱን ቀሪ ተግባራት በጊዜ የለንም ስሜት መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን