የካቲት ለምን የጥቁሮች ወር ተባለ?

67

ባሕር ዳር: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሰው መታየት የተነፈጋቸው ጥቁሮች ነጻነታቸውን እና መብታቸውን ለማግኘት እጅግ አስከፊ እና ዋጋ ያስከፈለ ትግልን እንዳካሄዱ በታሪክ ድርሳናት ተከትቦ ይገኛል። የነጻነት ቀንዲል የኾኑ ቆራጥ ጥቁሮች በከፈሉት ዋጋ ነጻነት ሊመጣ ችሏል። በርግጥ አሁንስ ቢኾን ጥቁሮች ነጻ ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ቢኾንም እንኳ። ዛሬም በዘር እና በቀለም ምክንያት ዓለም ላይ ያለው መድሎ ፍጻሜውን ያገኘ ግን አይመስልም።

የነጮችን የበላይነት ለማስቀረት እና የአፍሪካ አሜሪካውያን መብትን ለማስከበር ሲባል በርካታ ጥቁሮች ከፊት ኾነው በመታገል ዘመን አይሽሬ ታሪክ ጽፈዋል። የእነዚያ ታጋይ ጥቁሮች ታሪክ ሲወሳ ታዲያ ወርሐ የካቲት አብሮ ይነሳል። ትግላቸው ወርሐ የካቲትን የነሱ ታሪክ የሚዘከርበት ወር ኾኖ እንዲከበር እስከማድረግ የደረሰ ትግል ነበር ያደረጉት ማለት ይቻላል።

የብሔራዊ የጥቁሮች ታሪክ ወር መነሻው እንደ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1915 ነው። የታሪክ ምሁር እና ደራሲ የነበሩት ካርተር ጅውድ ሰን (ዶ.ር) የጥቁሮች ሕይዎት እና የታሪክ ጥናት የተባለ ማኅበርን በዓላማ የመሠረቱበት ወቅት እንደ ነበር ይነገራል። ይህ ድርጅት ዛሬ ላይ የአፍሪካ አሜሪካውያን ሕይዎት እና የውጭ ታሪክ ጥናት ማኅበር እየተባለ ይጠራል።

የጥቁሮችን የታሪክ ወር ማክበር ያስፈለገበት ምክንያት አፍሪካ አሜሪካውያን ለአሜሪካ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ትኩረት እንድያገኝ በማሰብ እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል። ታሪክ እንደሚነግረን በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ ለሄዱ እና በአሜሪካ ውስጥ ለሚኖሩ ጥቁር አሜሪካዊያን ሁሉ ወሩ የሚገባቸውን ክብር የሰጠ ነው ይባልለታል።

የጥቁሮች ታሪክ ወር በየ ዓመቱ የሚከበር የመታሰቢያ ወር ሲኾን የአፍሪካ አሜሪካውያን ወር እየተባለም ይጠራል። ይህ የጥቁሮች ታሪክ መታሰቢያ ወር በዩናይትድ ስቴትስ እና በካናዳ በየካቲት ወር በድምቀት ይከበራል። መከበሩም በመንግሥታቱ ዕውቅና የተቸረው ነው። በአየርላንድ እና በእንግሊዝ ደግሞ ታሪኩ የሚታወሰው በወርሃ ጥቅምት ነው።

የየካቲት ወር የጥቁሮች የታሪክ ወር እንዲኾን የተመረጠበት ዋናው ሁለት መሠረታዊ ነገሮች እንደኾኑ ይነገራል። እነሱም የካቲት 12 የፕሬዝዳንት አብርሐም ሊንከን የልደት ቀን መኾኑ እና የካቲት 14 ደግሞ የፍሬድሪክ ዳግላስ የልደት ቀን በመኾኑ እንደኾነ ይነሳል። ፍሬድሪክ ዳግላስ ሰዎችን ከባርነት ቀንበር ለማላቀቅ በእጅጉ የጣረ ሰው እንደነበር በታሪክ ተቀምጧል። አብርሐም ሊንከንም ቢኾን እንዲሁ።

የጥቁሮች ወር ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ ለነጻነት ሲባል የሚወሳ ወር ኾኗል። በ1976 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጀራልድ ፎርድ በታሪካችን ሁሉ ጥቁር አሜሪካውያን በተለያዩ መስኮች ያከናወኑትን ተግባር ለማክበር የጥቁሮችን የታሪክ ወር አስፈላጊነት በመረዳት በይፋ ወሩ እንዲከበር ያወጁበት ወቅት ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ ወሩ የጥቁሮች ወር ኾኖ እስካሁን እየተከበረ ይገኛል። የጎላ እንቅስቃሴ ባይደረግም ቅሉ በ1940 ዎቹ የጥቁሮች ታሪክ ጥናትን በትምህርት ቤቶች እና የጥቁር ታሪክ ክብረ በዓል ላይ በሕዝብ ፊት ለማስፋፋት ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበርም በታሪክ ተከትቧል። በደቡባዊው የአሜሪካ ክፍል ጥቁር መምህራን የዩናይትድ ስቴትስ ታሪክን እንደ ማሟያ አድርገው የጥቁሮችን ታሪክ ያስተምሩ እንደነበርም ታሪክ ያወሳል። በዚያ የግብግብ እና ነጻነትን የመሻት ትግል ግን ብዙዎች ዋጋ ይከፍሉ ነበር።

በጥቁሮች የታሪክ ወር ውስጥ ስማቸው ቀድሞ የሚነሳ ግለሰቦች አሉ። በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ውስጥ ከፍተኛ ትግል እንዳደረጉ የሚነገርላቸው ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር፣ በ1967 በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሾሙት የመጀመሪያው አፍሪካ አሜሪካዊ ዳኛ ቱርጉድ ማርሻል ተጠቃሽ ናቸው።

በተጨማሪም በ1992 ወደ ህዋ የሄደችው የመጀመሪያዋ አፍሪካ አሜሪካዊት የጠፈር ተመራማሪ ሜይ ጀምሰ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ሮዛ ፓርክስ፣ በ2008 በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጠው አፍሪካ አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። ባጠቃላይ የጥቁሮች ወር ለነጻነት ሲባል የታገሉ፣ ዋጋ የከፈሉ እና ነጻነት በሰው ልጆች ዘንድ እንዲገለጽ በተግባር የታተሩ ታላላቅ ሰዎችን በማሰብ በየዓመቱ የሚከበር የነጻነት ወር ነው።

አሁንም ድረስ ፍጹም የኾነ እኩልነት በሌለባት ዓለም ውስጥ ሰው በሰውነቱ ብቻ እንዲከበር እና እኩል እንደኾነ የታገሉ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች መከታ እና ጋሻዎች ብዙ ናቸው። ለሌሎች መብት ሲባልም ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ስፍር ቁጥር የላቸውም። የእነዚያ የዓለም እውነተኛ ሰዎች ታሪክ እና ማስታወሻ ታዲያ በወርሐ የካቲት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል።

የካቲት ወሩ ብሶት የወለዳቸው የዓለም ጥቁሮች፣ መገለል የሰለቻቸው ቆራጥ የዓለም ግለሰቦች የሚወሱበት ታሪካዊ ወር ተደርጎ ይዘከራል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወረዳዎች እና ከተሞች ዘላቂ ሰላማቸውን እንዲያሰፍኑ እየተሠራ ነው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
Next article“ለሰላም የዘረጋነውን እጅ ሳናጥፍ የልማት እና የሕግ ማስከበር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ