ኢትዮጵያ ከፍተኛ የደኅንነት እና ጥራት ደረጃዎችን አሟልቶ የተሠራ አዲስ የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት ይፋ አደረገች።

59

አዲስ አበባ: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በይፋዊ ሥነ ሥርዓቱ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስቴሮች እና ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኾነ የደኅንነት እና ጥራት ደረጃዎች አልፎ የተሠራ አዲስ የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት ይፋ መደረጉን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት አስታውቀዋል፡፡ በዛሬው ዕለት ይፋ የኾነው አዲሱ የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት ዜጎች ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት ሚስጥራዊ ሰነድ ብቻ የያዘ ሳይኾን የግለሰቡን አሻራ የያዘ፣ ኢትዮጵያን የሚገልጹ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መገለጫዎች እንዲኖሩት ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። ለአብነትም የሉሲ፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ የፋሲለደስ ግንብ፣ የአክሱም ሐውልት፣ በገጾቹ ውስጥ መካተታቸውን አብራርተዋል፡፡

የመጨረሻው የዓለማችን የቴክኖሎጅ ውጤት ነው ተብሏል። ኢ-ፓስፖርቱ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀ ሲኾን እጅግ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ፣ ለአጠቃቀም አመች እና ፈጣን ነው ተብሏል። ፓስፖርቱ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ለማፋጠን ሚናው የላቀ ስለመኾኑም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ተቋሙ ከፓስፖርት በተጨማሪ ለውጭ ዜጎች የሚሰጡ ቋሚ እና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ መታወቂያ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡

አዲሱ ፓስፖርት የዲፕሎማት፣ የሰርቪስ፣ የመደበኛ እና የውጭ ዜጎች የጉዞ ሰነድ ያካተተ ሲኾን ፓስፖርቱን የማምረት ሥራም ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጀመር ተጠቁሟል። በይፋዊ ፕሮግራሙ የተገኙት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አዲሱ ኢ- ፓስፖርት የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ የሚያደርግ፣ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል፣ ከጉዞ ጋር የሚያጋጥሙ ማጭበርበሮችን የሚያስቀር፣ ለዜጎች ምቹ እና ቀልጣፍ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል፣ የቴክኖሎጅ ሽግግርን ለማማጣት እና ሕጋዊ የሥራ እድል ለማግኘትም የሚያስችል ነው ብለዋል።

ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለሕጻናት የነርቭ እና ኅብረ ሠረሠር ሕክምና የሚሰጥ ማዕከል ተመረቀ።
Next articleየማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ።