ለሕጻናት የነርቭ እና ኅብረ ሠረሠር ሕክምና የሚሰጥ ማዕከል ተመረቀ።

28

አዲስ አበባ: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የሕጻናት የነርቭ እና ኅብረ ሠረሠር ሕክምና የሚሰጥ ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ ተመርቋል። ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ከ1925 ዓ.ም ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆዬ ተቋም ነው። ለወሊድ ብቻ የነበረው ሆስፒታሉ ከ300 በላይ አልጋዎች የሚኖሩት ባለ ሰባት ወለል ህንጻ ግንባታ ማስፋፊያ እያደረገ ነው። 22 የስፔሻሊቲ እና ሰብ ስፔሻሊቲ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ በማድረግ ፈጣን አገልግሎት ለኀብረተሰቡ በማድረስ ላይ እንደሚገኝ የሆስፒታሉ ሥራ አሥፈጻሚ ዶክተር ቴዎድሮስ አቡሌ ተናግረዋል። በዓመት ከ5 ሺህ የሚበልጡ ሕጻናት አዲስ በተገነባው ማዕከል አገልግሎት እንደሚያገኙ እና 400 የሚደርሱ ሕጻናት የነርቭ ቀዶ ጥገና እና ሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኀላፊ ዲክተር ዮሐንስ ጫላ የሕጻናት የነርቭ እና ኅብረ ሠረሠር ሕክምና ልህቀት ማዕከል ለሆስፒታሉም ኾነ ለከተማው ትልቅ የጤና አገልግሎት አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል። ለልህቀት ማዕከሉ ግንባታ እና የሕክምና መሳሪያዎች መሟላት ሙሉ ወጭውን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የሸፈነው ሪች አናዘር ፋውንዴሽን እንደኾነ ገልጸዋል ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ለሪች ፋውንዴሽን ምስጋና አቅርበዋል። የማዕከሉ ዕውን መኾን የቀዶ ሕክምና የሚጠብቁ ሕጻናት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል። ማዕከሉ በሪፈራል፣ በክፍያ፣ በጤና መድኅንም ኾነ በነጻ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት መኾኑንም አንስተዋል።
በየጊዜው ተጨማሪ የሕክምና ቁሳቁስ የሚጠይቅ ማዕከል በመኾኑ የበርካቶችን ርብርብ የሚፈልግ ነው ተብሏል።

አዲስ አበባ ሕጻናትን ለማሳደግ በአፍሪካ ምርጧ ከተማ የያዘችውን ራዕይ የሚያግዝ የልህቀት ማዕከል ነው ያሉት ደግሞ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ናቸው። ሆስፒታሉ ዘመኑን የሚዋጅ አገልግሎት የሚሰጥበት እንደሚኾን አምናለሁ ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዘጋቢ: ድልነሳ መንግሥቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የትምህርት ቤት ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
Next articleኢትዮጵያ ከፍተኛ የደኅንነት እና ጥራት ደረጃዎችን አሟልቶ የተሠራ አዲስ የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት ይፋ አደረገች።