
ባሕር ዳር: የካቲት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ፣ በአልማ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በለሚ ከተማ የተገነባው የካርል አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለ ሁለት ወለል የሕንጻ ግንባታ ተጠናቅቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ እና የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የእንሳሮ ወረዳ ዋና አሥተዳደሪ አከበረኝ ዓላማው በትብብር እና በቅንጅት የተሠራው ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀ መኾኑን ገልጸዋል። ግንባታው 13 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበተም ተናግረዋል። ወደፊትም ከማኅበረሰቡ ጋር በትኩረት በመሥራት ቀጣይነት ያለው ልማት ለማምጣት በትኩረት እንሠራለን ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበ አልማ የኅብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አልማ የሚሠራውን ሥራ መደገፍ እንደሚገባም አመላክተዋል። አካባቢያችን የሚለማው አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል። ሰላማችንን ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
የሰሜን ሸዋ ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ልማት በቅብብሎሽ እንደሚለማ ገልጸዋል።ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራችንን በጋራ ማስቀመጥ ችለናል ብለዋል። የቀድሞ መሪዎች ለሠሯቸው መልካም ሥራዎችም ሊመሠገኑ ይገባል ነው ያሉት። የትምህርት ቤት ግንንባታ እውን ሊኾን የቻለው የእንሳሮ ወረዳ ሕዝብ ለልማት ያለው አመለካከት ትልቅ በመኾኑ ነው ብለዋል። ሕዝቡ የሀሳብ፣ የገንዘብ እና የጉልበት ተሳትፎ እንዳደረገም ተናግረዋል።
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ለአካባቢው ዕድገት መፋጠን ያለው አሰተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት አሥተዳደሪው የወረዳው ሕዝብ ከመሪዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ከዚህ በላይ ወረዳውን ማልማት ይገባዋል ብለዋል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ሁሉም ማኅበረሰብ የተሳተፈበት የሕንጻ ግንባታ ተጠናቅቆ ማስመረቅ በመቻላቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በቀጣይ ወረዳው በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንደሚኾኑ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!