
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ሁሉም የመስኖ ተጠቃሚ ዞኖች ላይ የተከሰተውን ሁሉን አውዳሚ ተምች ለመከላከል ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ ሰብል ጥበቃ ልማት ባለሙያ አቶ ተፈራ ሰይፉ እንደነገሩን ሁሉን አውዳሚ ተምች ከሦስት ዓመት በፊት በሀገር ደረጃ ተከስቶ ነበር፤ አሁንም ጊዜ እየጠበቀ በክልሉ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡
ሁሉን አውዳሚ ተምችን ለመከላከል ተባዩ በጊዚያዊነት ከሚከሰት ተባይነት ወጥቶ በመደበኛ ተባይ ተይዞ እንዲሠራ እየተደረገ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
አሁን ላይ ተባዩ በቆሎ አምራች በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች መከሰቱን ገልጸው በባህላዊው የመከላከል ዘዴ ለመቆጣጠር እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ይህን ተባይ በዋናነት መከላከል የሚቻለው በባህላዊው እያሰሱ የመልቀምና የመግደል ዘዴ እንደሆነ የጠቀሱት ባለሙያው አንዳንድ በኩታ ገጠም የተዘሩ ሰብሎች ላይ ግን በኬሚካል ለመከላከል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ነው ያስታወቁት፡፡
የተከሰተው ተባይ በአንደኛው ዙር የመስኖ ማጠናቀቂያ በሁለተኛው ዙር የመስኖ ሥራ ጅማሮ ላይ በመሆኑ እስካሁን ጉዳት እንዳላደረሰም ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡ ሁለተኛ ዙር የመስኖ ሰብል በሚደርስበት ግንቦት መጨረሻ እና ሰኔ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በተኩረት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ተባዩ ራሱን መሬት ላይ ቀብሮ የሚቆይ በመሆኑ ማሳን አዘውትሮ በማሰስ በባህላዊው የመልቀም ዘዴ ወዲያውኑ ማጥፋት ላይ ማተኮር እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ችግሩ በሰፋባቸው ምዕራብ ጎጃም ዞን ሁለትጁን ነሴ ወረዳ፣ ሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ ወረዳ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች ለመከላከል ቢሮው ጥረት እያደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ