
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን መዋቅር በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራት የዘርፉ አፈጻጸም እና የቀጣይ ቀሪ ወራት የትኩረት አቅጣጫዎችን በሚመለከት የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡ በምክክር መድረኩ የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ በክልሉ ለተፈጠረው ሰላም ድርሻው የጎላ ነበር ተብሏል፡፡
በክልሉ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የሰላም እጦት ክልሉን ለከፋ ማኅበራዊ እረፍት ዳርጎት ቆይቷል ያሉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ ትኩረቱ ክልሉ ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መሥራት ነበር ብለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በውሥብሥብ ችግር እና በበርካታ ፈተናዎች መካከል እያለፈም በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ በትጋት እንደሠራ ገልጸዋል፡፡
በቀውስ ወቅት የሰላም ጋዜጠኝነት እና መፍትሄ ተኮር ዘገባዎች ኮርፖሬሽኑ የተመራባቸው መንገዶች እንደነበሩ ያነሱት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተግባራትም በትኩረት ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የተቋም ግንባታ፣ የሚዲያ ተደራሽነት እና የላቀ ይዘት መረጣ ሥራዎች ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጡ ተግባራት መከናወናቸውንም አብራርተዋል፡፡
አሚኮ የክልሉን ሕዝብ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ሕዝባዊ በዓላት በፈተና መካከል እየታለፈም በቀጥታ ስርጭት ከየአካባቢው ለአድማጭ ተመልካች ማድረስ ችሏል ያሉት አቶ ሙሉቀን በፈተና ወቅት በፅናት ቆመው እና ሙያዊ ሥነ ምግባር ተላብሰው ዋጋ እየከፈሉ ያገለገሉ ባለሙያዎቹ እና አመራሮች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይም አሠራርን ማዘመን፣ ለብዙኀን ጥቅም መሥራት፣ ብዝኀ ልሳን መኾን፣ ምዘናን መሠረት ያደረገ አሠራርን ማስፈን፣ ነገን ዛሬ መሥራት እና ውጫዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ አንስተዋል፡፡ በክልሉ አሁን የተገኘውን ተስፋ ሰጭ ሰላም ዘላቂ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ሚናው የጎላ ነው ያሉት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ቢሮ ኀላፊ ሙሉነህ ዘበነ ዘርፉ ተቋም ተሻጋሪ ትስስር መፍጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ከክልል እስከ ወረዳ ያለው የኮሙዩኒኬሽን መዋቅር ሙያዊ እና ቁርጠኛ ኾኖ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በቀውስ ወቅት ሕዝቡ መረጃ ከትክክለኛ ምንጭ በተከታታይ ይፈልጋል ያሉት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አዱኛ ጋሻው በክልሉ ያለው የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን መዋቅር ለሕዝቡ በየቦታው እየገባ መረጃ ሲያደርስ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥም ተሁኖ የተሰጠው መረጃ ሕዝብ ዕውነቱን እና ሐሰቱን እንዲለይ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
ለክልሉ ሕዝብ አሁንም ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና ተአማኒ መረጃ ማድረስ ያስፈልጋል ያሉት አቶ አዱኛ ጋሻው በየተቋማቱ ያሉ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር አፈጻጸም መረጃዎችን ማድረስ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ የተቋማት ኀላፊዎች እና መሪዎችም ሕዝብ የማወቅ እና መረጃ የማግኘት መብት እንዳለው በመገንዘብ መረጃ መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!