
አዲስ አበባ: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን የታክስ እና ጉምሩክ ሥርዓትን ለማዘመን ያለመ የልምድ ልውውጥ መድረክ ከክልል እና ከከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኀላፊዎች ጋር እያካሄዱ ነው። የልምድ ልውውጡ የጉምሩክ እና ገቢዎች መስሪያ ቤት ተግባራትን በመጎብኘት የክልል ኀላፊዎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እና አዳዲስ ተግባራት በክልሎች እንዲተገበሩ ለማበረታታት ያለመ ነው።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እንደገለጹት ይህ ልምድ ልውውጥ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ ያሉ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቶችን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ሚኒስትሯ የሀገርን ወጭ ለመሸፈን የታክስ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። በመኾኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የገቢ ሠብሣቢ ተቋማትን ማሻሻል እና ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በቀጣይም የገቢ አሠባሰብ ሂደትን በከፍተኛ ደረጃ በማዘመን ቀልጣፋ ለማድረግ ትኩረት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። ይህ የልምድ ልውውጥ መድረክ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የክልል የገቢ ቢሮዎች ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመገምገም እና ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሀሳብ ለመለዋወጥ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል ሚኒስትሯ።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ የተሳተፉ የክልል እና የከተማ አሥተዳደር የገቢዎች ቢሮ ኀላፊዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግቢ የተከናወኑ ተግባራትንም ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ራሄል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!