የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራው በምርት ገቢያቸው ላይ ጭማሪ እንዳመጣ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

32

ባሕር ዳር: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ በ2017 በጀት ዓመት ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለመሥራት አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል። ይህም በዞኑ እየተካሄደ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ለማጠናከር እና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

የመቄት ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ፋሲካ ሹመት እንደገለጹት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ከመጀመሩ በፊት አፈሩ በዝናብ ተሸርሽሮ ይሄድ ስለነበር ምርታቸው በእጅጉ ይጎዳ ነበር። አሁን ግን በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ ከተጀመረ በኋላ አፈሩ ሳይሸረሸር በመቆየቱ የተሻለ ምርት እያገኙ ነው።

በተለይም በውኃ ማስረጊያ የተጠራቀመውን ውኃ በመጠቀም በክረምቱ ወቅት ሰብላቸውን በማልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። የዋድላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጸጋየ ጉቸ በበኩላቸው፣ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ የዝናብን ኀይል በመቀነስ የአፈር መሸርሸርን ከማስቀረት በተጨማሪ ለክትር የሚተከሉ ተክሎች ቅጠል ለአፈር ማዳበሪያነት እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

በተጨማሪም ውኃውን አጠራቅመው በመጠቀም ሌሎች ተክሎችን ለማልማት እንደሚጠቀሙበትም ገልጸዋል። ይህም ዓመታዊ የምርት ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ አስችሏል። በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ባለሙያ ሄኖክ አስራት እንደገለጹት በተከታታይ ዓመታት እየተሠራ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ የመሥኖ ውኃ አቅም እንዲያድግ እና አዳዲስ የመስኖ አማራጮች እንዲፈጠሩ አስችሏል። ይህም በርካታ የመስኖ ልማት ሥራዎች በዞኑ እንዲለሙ እና ማኅበረሰቡ እንዲጠቀም አስችሏል።

በ2017 በጀት ዓመትም 21 ሺህ 192 ሄክታር መሬት ላይ አዲስ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየተሠራ ነው፡፡ 8 ሺህ 880 ሄክታር ላይ ደግሞ ነባር የደረጃ ማሳደግ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል። በተጨማሪም 7 ሺህ 859 ሄክታር የተጎዱ እና የተራቆቱ መሬቶችን የመከላከል እና የመጠበቅ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።

ለዚህም 676 ተፋሰሶች በዞኑ በሚገኙ 283 ቀበሌዎች ተለይተዋል ብለዋል። በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎችም ስልጠና ወስደዋል ነው ያሉት። በአብዛኛው ወረዳ እና ቀበሌዎች ከጥር 15/2017 ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ሥራው በሕዝብ ንቅናቄ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።

እስካሁን ባለው አዲስ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ከታቀደው 7 ሺህ 161 ሄክታር መሠራቱን የተናገሩት ባለሙያው 2 ሺህ 030 ሄክታር ነባር የደረጃ ማሳደግ ሥራ (23%)፣ 6 ሺህ 833 ሄክታር የመከለል እና የመጠበቅ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል። በሥራው ላይም ከ1 ሚሊዮን 805 ሺህ በላይ ወንዶች እና ከ887 ሺህ በላይ ሴቶች ተሳትፈዋል።

ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ይህ መሻሻል ሊመጣ የቻለው ከአምናው የፀጥታ ችግር ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ፣ በየደረጃው በተካሄዱ መድረኮች በተሻለ መግባባት ላይ በመደረሱ እና በዞን ደረጃ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በመደረጉ ነው ሲሉ ባለሙያው ገልጸዋል።

በተሠራው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ የአፈር ለምነት በመሻሻሉ እና ጎርፍ በመከላከል የሰብል ምርት እና ምርታማነት ዕድገት እንዲኖር እንዳስቻለ አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበበጀት ዓመቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next article“በበጀት ዓመቱ 111 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ገብተዋል” የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ