
አዲስ አበባ: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2017 ዓ.ም ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል። በግማሽ ዓመቱ የድንበር እና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ተጠቃሚነት፣ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እና አተገባበር፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ጥራት እና ፍትሃዊ ተደራሽነት ላይ በርካታ ተግባራት መከናወኑ ተገልጿል።
በዕለቱ የውኃ ሃብት አሥተዳደር እና አጠቃቀም፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ተቋማዊ የማሥፈጸም አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) ተናግረዋል። በከተማ እና በገጠር ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን በመድረኩ የተሳተፉ የክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች ገልጸዋል።
በተለይም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን በመለየት በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ረጅ ድርጅቶች ትልልቅ የውኃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ሥለመኾኑም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል። እንደ ሀገር “በበጀት ዓመቱ 460 ሺህ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ሲኾን እስካሁን ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን” የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገልጿል።
በድርቅ የሚጠቁ የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች አምስት ትልልቅ የውኃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ሲኾን ከነዚህም ሁለቱ ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!