
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የአደረጃጀት፣ የስያሜ እና የሎጎ ለውጥ ይፋዊ የማስተዋወቂያ እና የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የኮርፖሬሽኑ መሪዎች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።
የኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መብት አድማስ ኮርፖሬሽኑ ለላቀ ለውጥ እና ሁለንተናዊ ከፍታ የአደረጃጀት፣ የስያሜ እና የሎጎ ለውጥ ማድረጉን ገልጸዋል። በ2002 ዓ.ም የተመሠረተው ተቋሙ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ያለውን የገበያ ክፍተት ለመሙላት ታስቦ መኾኑን አንስተዋል። በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የጠጠር እና የአስፓልት መንገድ፣ ድልድዮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ሌሎች ግንባታዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።
ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በአሁኑ ጊዜ ከ13 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ፕሮጀክቶች ውል ወስዶ በግንባታ ሥራ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል። የባሕር ዳር ኮሪደር ልማትንም ውል ወስዶ እየሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል። እንደ ጋሸና ላሊበላ እስከ ሰቆጣ መንገድን እና የመሳሰሉ ሌሎች ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶችንም ለመሥራት በዝግጅት ላይ መኾኑን ገልጸዋል።
ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣትም ትምህርት ቤት ገንብቶ ማስረከቡን፣ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ለአቅመ ደካሞችን ቤት ጥገና ማድረጉን፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ ወገኖች የጤና መድኅን ሽፋን መስጠቱን ጠቅሰዋል። ከ672 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
የኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ኃይሌ አበበ የቀድሞው የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የአሁኑ ኅብር የኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲመሠረት የነበረውን የኮንስትራክሽን ጉድለት በመሙላት የመሠረተ ልማት ዘርፍን በማጠናከር የመንገድ ተደራሽነትን ለማሳደግ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል ያሉት ሰብሳቢው ፈተናዎችንም አልፏል ብለዋል። ሌሎች ያልደፈሩትን መልክዓ ምድሮችን ደፍሮ በመግባት እና በመሥራት ለሕዝብ እና ለልማት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱንም ገልጸዋል። ኮርፖሬሽኑ በሠራው መሠረተ ልማትም ገጠርን ከከተማ በማገናኘት መንግሥታዊ አገልግሎትን ለሕዝቡ ማድረስ እንደቻለ ገልጸዋል። ክልሉ ከዓመት ዓመት ላስመዘገባቸው ዕድገቶች ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም ተናግረዋል።
የውስጥ ፈተናዎች ያህልውናውን ተፈታተኑት እንደነበር የጠቀሱት አቶ ኃይሌ የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ከመክሰም ያዳነውን ማስተካከያ በማድረጉ ነው ብለዋል። ድርጅቱ አሁን ላይ ከ3 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ይዞ ወደ ኮርፖሬሽን ደረጃ ማደጉን አንስተዋል። በ2030 ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ከአፍሪካ ተመራጭ ለመኾን ራዕይ አስቀምጦ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ለዚህም የሠራተኞችን፣ የሥራ ኀላፊዎችን እና የባለድርሻ አካላትን እገዛ ይፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ: ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!