
እንጅባራ: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ለገቢ ማስገኛ ሕንፃ መገንቢያ የሚኾን 2 ሺህ 860 ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቧል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ የቦታውን ሳይት ፕላንን ለአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሊቀ መንበር አለቃ ጥላዬ አየነው አስረክበዋል።
ሕንጻው ከአባላት መዋጮ እና ከማኅበሩ ደጋፊዎች በሚሰበሰብ ገቢ የሚገነባ ነው ተብሏል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የመላው ኢትዮጵያውያን ሀብት በመኾኑ በገቢ አቅሙ እንዲደረጅ የሕንፃው መገንባት ጉልህ ሚና ይኖራዋል ብለዋል።የማኅበሩ የገቢ አቅም ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ ማኅበሩ ካለው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር ታይቶ የግንባታ መሬት መሰጠቱን ተናግረዋል። የሕንፃ ግንባታው እውን እንዲኾን ከተማ አሥተዳደሩ ከፈረሰኛ ማኅበሩ ጋር በቅርበት እንደሚሠራም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሊቀ መንበር አለቃ ጥላዬ አየነው ማኅበሩ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ያለ አንጋፋ ማኅበር ነው ብለዋል። የሕንፃው መገንባት የማኅበሩን ታሪካዊ እና ባሕላዊ ይዘት ጠብቆ ለማቆየት እና ይበልጥ ለማስተዋወቅ እገዛ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
ባለ 10 ወለል ሕንፃ ለመገንባት መታቀዱን ያነሱት አለቃ ጥላዬ መላው የማኅበሩ አባላት እና ደጋፊዎች ለግንባታው ስኬታማነት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation