
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የተቀናጀ የሀብት አጠቃቀም ሶፍትዌር የምረቃ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል። የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ሥራ አሥኪያጅ ቀለሙ ሙሉነህ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸውን ገልጸዋል።
የክልሉን የገጠር መንገድ ተደራሽነት ለማሳደግ ገደሉን በመሙላት፣ ጎባጣውን በማቅናት፣ ወንዙን በመግራት የገጠሩ ኅብረተሰብ የትራንስፖርት ተጠቃሚ እንዲኾን ሠርቷል ነው ያሉት። በመንገድ ግንባታ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የመሥራት እና የመጠገን ሥራ መሥራታቸውንም ገልጸዋል። የመንገድ ልማት ለሁሉም ልማት ተደራሽነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ልማት ግንባታ ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የለማው ሶፍትዌር አሠራርን እንደሚያቀላጥፍ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ነው ያመላከቱት። የመንግሥትን ሀብት እና ንብረትን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችልም ገልጸዋል። የለማውን ዲጂታል ቴክኖሎጂም በዘላቂነት ለመጠቀም ቁርጠኞች መኾናቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ቴክኖሎጂን በመንገድ ዘርፉ መጠቀም ዘርፉን በተቀናጀ አሠራር ለመምራት ያስችላል ነው ያሉት። ወጭ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋ፣ ከንክኪ ነጻ የኾነ እና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያስችላል ብለዋል። ፕሮጄክቶችን በጊዜ ጀምሮ በጊዜ ለመቋጨት እንደሚያግዝም ተናግረዋል። ቴክኖሎጂን መጠቀም ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው የሀብት እና የሰው ኀይል አሥተዳደር እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት። ቴክኖሎጂውን ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲለማ እንደሚሠራም ገልጸዋል። የክልሉን የመንገድ ተደራሽነት ለማስፋት በተሻለ አሠራር መደገፍ እንደሚገባም አንስተዋል። ቴክኖሎጂን እያለሙ እና ከሁኔታዎች ጋር እያጣጣሙ መሄድ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ቴክኖሎጂ በጊዜ ሂደት እየለማ እንደሚሄድም አንስተዋል።
ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል። በቀጣይ ዘላቂነት ያለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲኖር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!