
ደብረ ማርቆስ: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለሁለተኛ ዙር ያሠለጠናቸውን የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ አባላት በደብረ ማርቆስ ከተማ አስመርቋል። በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ይሄነው አበባው ተመራቂዎች በሥልጠና ያገኙትን አቅም በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማጽናት እንዲሠሩ አሳስበዋል። ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሕዝብ እና መንግሥት የጣለባቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አንሙት ገላነህ የከተማ አሥተዳደሩን ሰላም የተሟላ ለማድረግ እና ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ የተጀመሩ ሕግን የማስከበር ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ተመራቂ የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ አባላት በዚህ በኩል ጉልህ ድርሻ አንደሚኖራቸውም አመላክተዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ተመራቂ የሚሊሻ አባላት ለሕዝብ በመታመን እና ከሕዝብ ጎን በመቆም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መትጋት እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት። ኅብረተሰቡን ለበርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የዳረገው የጸጥታ ችግር መቋጫ እንዲያገኝ እርስ በእርስ ከመጠፋፋት አዙሪት ፈጥኖ መውጣት ይገባልም ብለዋል፡፡
ፈተናዎችን በመጋፈጥ ለዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም አሳስበዋል። ተመራቂ የሚሊሻ አባላት የአካባቢያቸውን እና የሕዝባቸውን ሰላም ለመጠበቅ እና በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ የገቡ ወንድሞቻቸውን ወደ ሰላም መንገድ ለመመለስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም አመላክተዋል።
የተገኘውን ሰላም በማጽናት ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ገልጸዋል። የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሕግን የማስከበር ተልዕኳቸውን እንዲሚወጡም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!