
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኅብር የኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የአደረጃጀት፣ የስያሜ እና የሎጎ ለውጥ ይፋዊ የማስተዋወቂያ እና የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በመርሐ ግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር እና የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ኮርፖሬሽኑ ከነበረበት ችግር እንዲወጣ የአመራር፣ የአሠራር እና ሌሎችም ለውጦች ተደርገው እንደገና እንዲያንሠራራ እና ውጤታማ እንዲኾን ላደረጉት ለመላው ሠራተኞች፣ ለቦርድ አባላት እና ለሌሎች አጋሮች ምሥጋና አቅርበዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ ኮርፖሬሽኑ የስም ለውጥ ብቻ ሳይኾን በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ስትራቴጅካዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል። የቴክኖሎጂ እና የሥራ ባሕል እና ሂደት ለውጦች አስፈላጊነትንም አንስተዋል።
ኮርፖሬሽኑ በርካታ ውጤት ያመጣባቸው ዘርፎች የመኖራቸውን ያህል አሁንም በትኩረት ለውጥ ሊያመጣባቸው የሚገቡ እንዳሉም ገልጸዋል። የአመራር ዘይቤን እና የሥራ እሴትንም በአብነት አንስተዋል። የመወዳደር አቅምን በማሳደግ በገበያ መርህ በመመራት ለመሥራት መዘጋጀት እንደሚገባ የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ኮርፖሬሽኖች እና ኩባንያዎች ከመንግሥት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትም በገበያ ሕግ እንዲኾን እንፈልጋለን ነው ያሉት። ለዚህም በዋነኛነት አመራር ላይ ማተኮር እንደሚገባ አመላክተዋል።
ንጹህ የአትራፊ ተቋም ሠራተኛ መፍጠርም በትኩረት መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል። ስያሜዎች እና ሎጎዎችንም የንግድ እና የአትርፎ አደር ተቋም ማድረግም ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥትም የገበያ ሕጉን ባከበረ መልኩ የማገዝ ኀላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!