አልማ በደብረ ማርቆስ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

34

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን አልማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በደብረ ማርቆስ ለሚገኙ በስምንት ትምህርት ቤቶች ከ390 በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ከመስከረም ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ከጀኔቫ ግሎባል ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ለትምህርት የደረሱ እና ትምህርት የማያገኙ እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆችን በመደገፍ የተፋጠነ ትምህርት እንዲያገኙ እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አልማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘላለም አንዳርጌ ገልጸዋል።

ጽሕፈት ቤቱ በከተማዋ ለሚገኙ ከ390 በላይ ተማሪዎች 800 ደርዘን ደብተር እና በአልማ የተፋጠነ ትምህርት ፕሮጀክት ለታቀፉ ስምንት ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ኀላፊው ተናግረዋል። አልማ የትምህርት ቤቶች ደረጃ እንዲሻሻል እና የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሚገኝም አቶ ዘላለም አስረድተዋል።

ድጋፋ ከተደረገላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የኾነው የአብማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ትጓደድ ንጉሤ ድጋፍ መደረጉ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ውጤታማነት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል። በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን የገለጹት ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ውጤታማ ለመኾን እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ያምራል ታደሰ አልማ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እና የተፋጠነ የትምህርት ትግበራ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ በመኾኑ ምሥጋና አቅርበዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን አልማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከ750 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ከጽሕፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተቋማት የሚገነቡት ችሎታና ፍላጎት ሲጣጣሙ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“በራስ አቅም ተወዳዳሪ ኾኖ መዝለቅ ከኮርፖሬሽኖች ይጠበቃል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ