
ባሕር ዳር: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የተቀናጀ የሀብት አጠቃቀም ሶፍትዌር የምረቃ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል። በሥነ ሥርዓቱ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ባለፉት ዓመታት የአማራ ክልል የገጠር መንገድ ጥያቄ እንዲመለስ እና የመንገድ ተደራሽነት እንዲሻሻል መሥራቱን ገልጸዋል። ልማትን በማሳለጥ ሁነኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።
ሌሎች ተቋማት በማይደርሱባቸው አካባቢዎች እየደረሰ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል። የኤጀንሲው መሪዎች እና ባለሙያዎች መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ለመንገድ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ነው ያሉት። አሁንም የክልላችን ሕዝብ ዋነኛ ጥያቄ የመንገድ መሠረተ ልማት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ ለመንገድ መሠረተ ልማት እና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ልዩ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል። የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄን ለመመለስ ሁለንተናዊ ለውጥ እና ሰፊ ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ኤጄንሲው የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄ እንዲመለስ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል።
የለማው ቴክኖሎጂ ሀብትን በአግባቡ ለማሥተዳደር እና ሥራን በአግባቡ ለመምራት እንደሚያስችል ነው ያነሱት። የለማውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ መተግበር እና መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል። መሪዎች እና ባለሙያዎች የለማው ቴክኖሎጂ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲኾን ትኩረት እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።
ቴክኖሎጂን በዘላቂነት በመጠቀም የሕዝብን እርካታ ማሳደግ እና ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት። ቴክኖሎጂውን ስላበለጸጋችሁ እውቅና እንሰጣችኋልን ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ የበለጠ እውቅና የምንሰጣችሁ ግን በዘላቂነት ስትጠቀሙት ነው ብለዋቸዋል። መንግሥት በስፋት የሚጠየቅበትን የመንገድ ዘርፍ በትኩረት መምራት እንደሚገባም አሳስበዋል። የሥራ ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ወጪን ለመቀነስ፣ ሀብትን በአግባቡ ለማሥተዳደር እና ሥራን በቅልጥፍና ለመምራት ያስችላል ነው ያሉት።
“ተቋማት የሚገነቡት ችሎታና ፍላጎት ሲጣጣሙ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ በፍላጎት እና በችሎታ መካከል ክፍተት ካለ የሚፈለገው ስኬት አይገኝም ብለዋል። ባለሙያዎች እና መሪዎች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ባለሙያነት የሚረጋገጠው የተሰጠን ሙያ በአግባቡ መወጣት ሲቻል ነው ብለዋል።
ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲያመጡ እና ዘላቂነትን እንዲያረጋግጡ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። ተቋሙ ለክልሉ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አንስተዋል። የክልሉን ሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ ለመፍታት ኀላፊነትን በአግባቡ መወጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የክልሉ ሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ ልማት እና መልካም አሥተዳደር መኾኑንም ገልጸዋል። የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄ እንዲመለስ ደግሞ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ክልሉን ለመለወጥ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን