
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከልክ ያለፈ ፍርሃት እና የበዛ ግዴለሽት በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ላይ ተፅዕኖ ይዞ ይመጣል፡፡ ሁለቱም የሰው ልጅ ባሕሪዎች በዚህ የኮሮና ቫይረስ ወርረሽ ወቅት ትልቅ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡
ከነዚህ ባሕሪዎች ለመውጣትና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ደግሞ ሰዎች የሚፈሩትን ነገር ትክክለኛ መረጃ ወደ አእምሯቸው ማስገባት ላይ ሊሠራ እንደሚገባም የሥነ ልቦናምሁራን ይመክራሉ፡፡
የሚታየን የበዛ ፍሃትና የበዛ የግድየለሽነት ባሕሪ ለማስወገድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የዓለም የሕክምና ጠበብቶች ለቫይረሱ ክትባት ለማግኘት ደፋቀና እያሉ ቢሆንም የቫይረሱ የመዛመት ፍጥነት ትንፋሽ የሚሰጥ አልሆንም፡፡ ከችግሩ ያላመለጠችው ኢትዮጵያም መፍራት ሳይሆን መጠንቀቅ እና መከላከል ላይ በመሥራት የተጠመደች ቢሆንም አሁንም በዜጎች ላይ የሚታየው የበዛ ፍርሃት እና የበዛ ቸልተኝነት የሚያመጣው ቀውስ ውሎ አድሮ ዋጋ እንደሚያስፍል ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው እና የጉብኝት ባለሙያው ተሾመ አየለ (ተሸ ባላገሩ) ተናግረዋል፡፡
የሥነ ልቦና መምህሩ አቶ ሄኖክ አየለ ደግሞ ‘‘ፍርሃት በባሕሪው ጠቃሚ ቢሆንም ሲበዛ ደግሞ ጉዳት ይዞ ይመጣል፤ ከዚህ ለመውጣት ደግሞ ሰዎች የሚፈሩትን ነገር ትክክለኛ መረጃ ወደ አእምሯቸው ካለማስገባት የሚመጣ በመሆኑ ትክክለኛ መረጃን ከትክክለኛ ምንጭ በመውሰድ እና መደናገርን በማስወገድ ራስን መጠበቅ ይቻላል’’ ብለዋል፡፡
በሰዎች መካከል የሚታየው የበዛ ለነገሮች ትኩረት ያለመስጠት ባሕሪን ለመቀየር ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ በመንግሥት በኩል የእርምት ርምጃ መውሰድ ተገቢ መሆኑንም ይመክራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊነት ላይ ሊሠራ እንደሚገባ ነው የሥነ ልቦና ምሁሩ ያሳሰቡት፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን -ከአዲስ አበባ