“የእርሻ ውል ሥርዓት ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ድርሻው ከፍተኛ ነው” አቶ አጀበ ስንሻው

30

ባሕር ዳር: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ውል እርሻን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። የግብርና ምርት ውል በአምራቹ እና በአስመራቹ መካከል የሚኖር የግብርና ምርት አመራረት ሂደት እና ስምምነትን የሚመለከት ተግባር ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የእርሻ ውል እንደ ክልል ከተጀመረ የቆየ ቢኾንም ከአስፈላጊነቱ አንጻር ግን የበለጠ መጠናከር ያለበት ነው ብለዋል። የእርሻ ውል ሥርዓት ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ድርሻው ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል። በአስመራቹ እና በአምራቹ መካከል ሕግን መሠረት ያደረገ ውል ካለ መልካም ግንኙነት ይኖራል ነው ያሉት።

ተግባሩ የመንግሥትን ጫና በመቀነስ ረገድም ጥቅም አለው ብለዋል። በእርሻ ውል ሥርዓት መመራት የገበያ ሰብሎችን በዘመነ መንገድ እንዲመረቱ በማድረግ በኩልም ከፍተኛ ድርሻ አለው ነው ያሉት። ይህ ሲኾን ታዲያ አምራቹም ኾነ አስመራቹ በዕውቀት የሚመሩት ኾኖ ሊገኝ ይገባልም ብለዋል። የእርሻ ውል የማምረት ሂደት ሕግ እና ሥርዓት ተበጅቶለት የሚመራ መኾኑንም አቶ አጀበ አስገንዝበዋል።

አስመራቹም ኾነ አምራቹ በገቡበት የውል ስምምነት መሠረት ማምረት ይኖርባቸዋል ብለዋል። ከተገባው ስምምነት ውጭ የሚያስመርትም ኾነ የሚያመርት ይጠይቃል ነው ያሉት። በውይይት መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ተገቢ የኾነ ሕግ ለልማት መሳለጥ አዋጭ ተግባር እንደኾነ ተናግረዋል።

ሕግ ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር ረገድ አጋዥ ሊኾን እንደሚገባ ገልጸዋል። የእርሻ ውል ስምምነትም ሕግ እና ሥርዓት ያለው ነው ብለዋል። በእርሻ ውል ስምምነት መሠረት ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር በሚደረገው ጥረት መሐል ላይ የሚገቡ ደላሎች እንቅፋት መኾናቸውን አንስተዋል።
ያለአግባብ መጠቀም የሚፈልጉ ደላሎች መጠየቅ እንዳለባቸውም አንስተዋል።

የእርሻ ውል ስምምነቱ ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ቢኾንም ተጠያቂነቱን ጭምር ማወቅ ግን ከአምራቹም ኾነ ከአስመራቹ የሚጠበቅ ነው ብለዋል። ጉዳዩ የአምራች እና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የወጣ እና በአዋጅ ቁጥር 1289/2015 ላይ የተደነገገ ተግባር ነው።

ዘጋቢ ፦ ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማስፋፋት ለምናልመው ብልፅግና ወሳኝ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የተቀናጀ የሀብት አጠቃቀም ሶፍትዌር የምረቃ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።