“ስለትምህርት ዝም ማለት በትውልድ ላይ መዝመት ነው”

35

ባሕር ዳር: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብቻውን መቆም የሚችል፣ ምክንያታዊ የኾነ፣ ቀናውን መንገድ የሚከተል፣ ንድፈ ሃሳባዊ ብቻ ሳይኾን በተግባር ተፈትኖም የሚያልፍ ትውልድ የሚሠራበት ብቸኛው ማዕከል ትምህርት ነው፡፡ በደቦ የሚሠራ እንጅ በደቦ የማያስብ፣ ድምዳሜው በጭፍን ሳይኾን በጭብጥ ላይ የተመሠረተ፣ በጅምላ የማያወግዝ፣ ነሲቡን የማያሞካሽ እና መርምሮ የሚፈርድ ትውልድ የሚሠራው በትምህርት እና በትምህርት ብቻ ነው፡፡

ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትሠራ እርስት ስትኾን በየዘመኑ የሚያልፍ ትውልድ ግንበኛ፤ ዘመኑን የሚዋጅ ሥርዓተ ትምህርት አንጠረኛ ኾነው ይገነቧታል፡፡ በፈጠራ የተራቀቁ እና በምጣኔ ሀብታዊ ደረጃቸው የመጠቁ ሀገራት የዕድገታቸው ሚስጥር ለትምህርት ልማት በሰጡት ትኩረት ልክ የተገነባ ነው፡፡
የረጅም ዘመን እና ጥንታዊ የትምህርት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓቷ ትውልድ የሚገነባ እና ሀገር በቀል እንደነበር ይነገራል፡፡

ዓለም አቀፍ እሳቤን የተላበሱ፤ የሀገራቸውን ችግር የሚፈቱ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች የሚፈልቁባት ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትምህርት ሥርዓቷ ስብራት ገጥሞት ቆይቷል የሚሉት የበዙ ናቸው፡፡ የሥርዓተ ትምህርት ችግሩ ርዕዮተ ዓለማዊ ስህተት እና ምሁራዊ ቸልተኝነት ተደማምረውበት ትውልድን እንደ ደጋን ያጣመመ፤ ሀገርን እንደ ኩሬ ያቆመ ከሚኾንበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሁን ደግሞ ከነጭራሹ መማር ፈተና ላይ የወደቀበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

አንድ ወቅት ከአሚኮ ጋር የስልክ ቆይታ የነበራቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ትምህርት የመጨረሻ ግቡ አንጻራዊ ዕውቀት፣ ሙያዊ ክህሎት እና ሰዋዊ ግብረ ገብነት የተላበሰ ትውልድ መገንባት ነው ይላሉ፡፡ የትምህርት ግብ የመጨረሻ ልኬት በሁለንተናዊ መመዘኛው ብቁ የኾነ ትውልድ መገንባት ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መንገሻ የትምህርት ሥርዓታችን ስብራት የሚገለጠውም በዚህ ነው ይላሉ፡፡ ዘርፉ ብቁ የኾነ ዜጋ የማፍራት ራዕይ እና ትልሙ የኾነ ዘመን እና ጊዜ ላይ ስብራት ገጥሞታል ባይ ናቸው፡፡

ትውልድ እንደ ችግኝ ከመጀመሪያው የዕድገት ደረጃ ጀምሮ እንክብካቤን እና ክትትልን ይፈልጋል፡፡ የተዛባ የዕድገት ደረጃ እና ሂደት ለተዛባ ትውልድ ምክንያት ይኾናል፡፡ አሁን ላይ ሀገር የገጠማት ዙሪያ መለስ ችግር አንድ ወቅት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተፈጠረ ስብራት እንደኾነ እሙን ነው፡፡ ችግሩ ከትምህርት ሥርዓቱ አልፎ የሀገርን ህልውናም የሚገዳደርበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

አማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ50 በመቶ በላይ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት እና በተለያየ የክፍል ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸው እንዲቋረጥ ተገድደዋል፡፡ ከ300 በላይ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው፡፡ ይህ ከትናንቱ የትምህርት ስብራት በዘለለ ዛሬ ላይ በትውልድ ስብራት የተቃጣ ምልክት ነው፡፡

የክልሉ ትምህርት ፈውስ እና ወጌሻ የሚያሻው ኾኗል፡፡ ትናንት ድክመት እና ጉድለት አለበት የሚባለው ትምህርት ዛሬ ከእነጭራሹ ሕልውናው አደጋ ውስጥ ገብቷል፡፡ ዘመንን የዋጀ፣ በልምድ የደረጀ እና ባለድርሻዎችን ያቀናጀ ንቅናቄ ከወላጆች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ግድ ብሏል፡፡ ስለትምህርት ዝም ማለት ትውልድን መግደል እና በትውልድ ላይ መፍረድም ነው፡፡

በታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በወልድያ ከተማ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
Next articleከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።