የኮሮና ወረርሽኝ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ አካል ጉዳተኞችን ሕይወት እየፈተነ ነው፡፡

132

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ሰማኸኝ ሞላ ዓይነ ስውር ናቸው፡፡ ለሥራ ያልደረሱ የሁለት ልጆች አባትም ናቸው፡፡ ቤተሰባዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡት የክብደት መለኪያ ሚዛን መንገድ ላይ አስቀምጠው በሚያገኟት ዕለታዊ ገቢ ነው፡፡ ነገን ከዛሬ የተሻለ ለማድረግ ይተጉ የነበረው አቶ ሰማኸኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የእርሳቸውና የሚያስተዳድሯቸው የቤተሰብ አባላት ሕይወት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጋርጦባቸዋል፡፡

እንደ አቶ ሰማኸኝ አስተያየት ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ሰዎች በብዛት ይመላለሱባቸው የነበሩ የባሕር ዳር አውራ መንገዶች ፍሰት ቀንሷል፡፡ አልፎ አልፎ የሚንቀሳቀሱ መንገደኞች እንኳን ቢኖሩ እንደ በፊቱ ክብደታቸውን አይለኩም፤ ቢለኩም እንደ ድሮው ተመላሽ ሳንቲሞችን ትተው የሚሄዱት በቁጥር አናሳ ናቸው፡፡ “ኧረ ከባድ ነው፤ በሽታው መከሰቱ ከተነገረ ጀምሮ መንገድ የሚያሻግረን ሰው እንኳ እያጣን ነው!” በማለት ወረርሽኙ በኑሮሯቸው መስተጋብር ላይ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ አብራርተዋል፡፡

በእርግጥ በሽታው በሁሉም የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እያስከተለ ነው፡፡ የሰውን እጅ ተማምነው የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት በሚዳዱ አካል ጉዳተኞች ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ጫና ግን የከፋ እንደሆነ ተናግረዋል፤ መሪ እስከማጣት መቸገራውንም ገልጸዋል፡፡ ምሥጋና ወገናዊ አለኝታቸውን በተግባር እያሳዩ ላሉ ባለሀብቶች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መረዳዳት፣ መደጋገፍንና የወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር እየታየም ነው፡፡

አቶ ሰማኸኝና ቤተሰቦቻቸውም ለዕለት ቢሆንም አሳቢ፣ አይዞን ባይ አግኝተዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው ቤተ ዳንኤል ሆቴል ችግራቸውን ግምት ውስጥ አስገብቶ የምግብ ዘይት፣ የዳቦ ዱቄትና የንጽሕና መጠበቂያ ሳሙና ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ ሆቴሉ ከ30 ሺህ ብር በላይ ወጭ አድርጎ 70 ለሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ዛሬ የዕለት ጉርስ ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡

ቤተ ዳንኤል ሆቴል ከዚህ በፊት በከተማ አስተዳደሩ ለተቋቋመው የኮሮና መከላከል ኮማንድ ፖስት የ30 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉንም የፋሲሎ ክፍለ ከተማ አፈ ጉባኤ ዘለቀ ገበየሁ አስታውሰዋል፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የሚሆን 150 ብርድ ልብሶችን ገዝቶም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ማስረከቡንም ከሆቴሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

አስከፊ ወቅት ለመረዳዳት እና ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን በተግባር እንዲገለጡ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ደጋግ ልቦች ያፈለቋቸው ደጋግ ሐሳቦች የብዙዎች ሕይወት እንዲቃና እያደረጉም ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous articleበግብርና ልማቱ የሚያጋጥሙ የግብዓት አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር እና የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የሰሞኑ ጉብኝት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ተናገሩ።
Next articleፍርሃትና ግዴለሽነት ዋጋ እንዳያስከፍሉ መጠንቀቅና የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ባለሙያዎች አሳሰቡ፡፡