የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከ1 መቶ 11 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

35

አዲስ አበባ: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡ በምክር ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን ሪፖርት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በስድስት ወሩ ለ1 መቶ 50 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 1 መቶ 42 ሺህ 908 ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማሳደግም ባለፉት ስድስት ወራት 7 መቶ 25 ሚሊዮን 4 መቶ 80 ሺህ 8 መቶ 10 ቶን ተኪ ምርት በማምረት ከ4 መቶ 90 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማዳን መቻሉንም ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አንስተዋል። ከገቢ አንፃርም 1 መቶ 25 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 1 መቶ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የዕቅዱን 90 በመቶ በስድስት ወሩ መሠብሠቡንም ገልጸዋል።

ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በጥራት እና ፍጥነት መሥራት መቻሉን በጥንካሬ ያነሱት ከንቲባ አዳነች በተያዘላቸው በጀት እና ጊዜ ያልተጠናቀቁትን ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ከሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት አኳያ አጠቃላይ ስፋቱ 3 ሺህ 5 መቶ 15 ሄክታር የሚሸፍን እና 1 መቶ 35 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ፣ የብስክሌት፣ የእግረኞች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም መሠረተልማትን ጨምሮ ሌሎችንም ያካተተ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በማኅበራዊ ዘርፎች በጤና እና ትምህርት እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በተሠሩ ሥራዎች ውጤት መመዝገቡንም በሪፖርቱ ላይ ተመላከቷል። ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ሀሳብ እና ጥያቄዎች ቀርበው በከንቲባዋ ምላሽ እየተሰጠበት ሲኾን ምክር ቤቱ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የሠራተኞች መተዳደሪያ አዋጅ እና የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ማዕከልን መልሶ ማደራጀት አዋጅን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዘመኑን የዋጁ እና ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው ለሚሠሩ ወጣቶች ዕውቀታቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እገዛ መደረግ አለበት” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next articleሩሲያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም አፈጉባኤ ታገሠ ጫፎ ገለጹ።