“ዘመኑን የዋጁ እና ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው ለሚሠሩ ወጣቶች ዕውቀታቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እገዛ መደረግ አለበት” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

35

ደሴ: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወር የሥራ አፈፃፀም ግምገማን በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ይትባረክ ጌታሁን ባለፉት ስድስት ወራት ከ10 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል በተለያዩ የሥራ ዘርፎች መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ አሰፋ ይልማ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያግዝ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ፈንድ መፈቀዱን ገልጸዋል። በክልሉ ባሉ 246 ኮሌጆች የተግባር ሥልጠናዎችን በመስጠት ብቁ የኾነ የሰው ኀይል ለመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከማቅረብ አኳያ ቢሮው አይነተኛ ሚናን እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ባለፉት ሰባት ወራት 5 መቶ 10 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት። በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) “ዘመኑን የዋጁ እና ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው ለሚሠሩ ወጣቶች ዕውቀታቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እገዛ መደረግ አለበት ብለዋል።

የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በቋሚ እና በጊዜያዊ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በግምገማ መድረኩ ላይ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን፣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:-ሠልሀዲን ሰይድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ያቆዩት በመሥዋዕትነት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከ1 መቶ 11 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።