
ባሕርዳር: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለየካቲት 12 የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ ቀን የእንኳን እረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ያቆዩት በመሥዋዕትነት ነው። ያውም ከውስጥ ባንዳና ከውጭ ባዳ ጋር እየታገሉ ብለዋል።
በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ጣልያን ወረራ ጊዜ ዐርበኞች ለነጻነት እና ለሉዓላዊነት ይታገላሉ። ባንዳዎች ደግሞ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ከጠላት ጋር ተባብረው ሀገራቸውን ይወጋሉ። ያስወጋሉ ነው ያሉት። ባንዶች ይሄንን የሚያደርጉት ሕዝባቸውን ሽጠው የልብስ እላቂ እና የወርቅ ድቃቂ ለማግኘት ነው። የሀገር ጠላት በመጨረሻ እነርሱንም እንደማያተርፋቸው ያውቃሉ። አጋምን የተጠጋ ቁልቋል ዘላለም ሲያለቅስ ይኖራልና ብለዋል።
ዛሬም ባንዳዎች አሉ። ለግል ጥቅማቸው ከምንጊዜም የሀገር ጠላት ጋር አብረው የገዛ ሀገራቸውን የሚወጉ። ሆድ ከሀገር ፣ ሥልጣን ከሕዝብ የበለጠባቸው ነው ያሉት። አስደሳቹ ነገር ግን ዛሬ ከባንዳዎቹ የዐርበኞቹ ቁጥር ይበልጣል። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ፣ ፈተናውን ሁሉ እያሸነፈች በሁለንተናዊ ብልጽግና ጎዳና ላይ የምትራመደው ብለዋል።
ከእናትና አባት ዐርበኞች የተማርነው ራስን ሠውቶ ሀገርን ማኖር እንጂ ሀገርን ሠውቶ ራስን ማኖር አይደለም። ሰማዕትነታችሁን አንዘነጋውም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!