
ወልዲያ: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከራያ ቆቦ ወረዳ እና ከቆቦ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቆቦ ከተማ ምክክር አድርገዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በቱባ ባሕሉ የሚታወቀው የራያ ሕዝብ ባሕሉን እና ወጉን ለማስተዋወቅ ሰላም እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።
ነገ ወደ ሃብት ሊቀየር የሚችል ወርቃማ እሴታችሁ እንዳይሸረሸር የተቋጠረውን የሰላም ማነቆ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል። በችግር ውስጥ ኾነን በልማት መራመድ አይቻልም ያሉት አፈ ጉባኤዋ መከላከያ ሠራዊት ሰላማችሁን ለመጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ በመኾኑ ልትደግፉት ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ዝግጁ ነው፤ ይህን ዕድል መጠቀም ደግሞ ግድ ነው ብለዋል።
አንድ ባለመኾናችን እየተጎዳ ያለው ትውልድ ነው ያሉት አፈጉባዔዋ ልጆቻችንን ማስተማር አለመቻል የሚተካንን ትውልድ ወደ ቁልቁለት ጉዞ መምራት ነው ብለዋል በመልዕክታቸው። ጠበንጃ የያዙ ልጆቻችንም ጫካ ገብተው ማለቅ የለባቸውም፤ የመንግሥት የሰላም አማራጮች ውጤታማ እንዲኾኑ ከልባችሁ ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
“የሰላሙም ኾነ የልማቱ ቁልፍ ያለው በሕዝብ እጅ ነው” ብለዋል። የጥፋት ጎዳናን ለመዝጋት በትብብር መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። አካባቢው ሊለማ የሚችል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እና ሰፊ ዕድል ያለው ነው፤ ሊያለማው የሚችልም አቅም ያለው ትውልድ አለ፤ ሕዝቡ የአካባቢውን ጸጋ ከአልሚው ትውልድ ጋር በማቆራኘት ራሱን እና ከተማውን የማበልጸግ ተግባር ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የማንነት እና የወሰን ጥያቄ የሁላችንም ጥያቄ ነው ያሉት አፈጉባዔዋ የሚፈታውም በሁላችንም የጋራ ትብብር ነው ብለዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕጋዊ መልኩ ለመፍታት ብዙ ጊዜ ያቅዳል፤ ግን ዕቅዱ እንዳይፈጸም የሰላም መደፍረሱ እያደናቀፈ መኾኑን ነው ያነሱት። ይህ አደናቃፊ ኃይል የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስ አይፈልግም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!