“ሰላም የሀቀኛ ንግግር ውጤት ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

37

ወልድያ: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከራያ ቆቦ ወረዳ እና ከቆቦ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በቆቦ ከተማ ምክክር አድርገዋል። በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የራያ ሕዝብ ካለፉት መንግሥታት ጀምሮ ልጆቹን በሴራ ሞት የተነጠቀበትን ሁነት ሊመረምር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የራያ ሕዝብ ልማት እና ሰላምን ይፈልጋል፤ ሰላም ደግሞ የሀቀኛ ንግግር ውጤት ነው፤ በልማት ጥያቄ የተደበቀ ለቅሶ ሳይኾን እውነተኛውን የልማት እንቅፋት ዙሪያ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል። “ከልባችሁ አልሠራችሁበትም እንጂ ጥሩ የግጭት መፍቻ መንገድ አላችሁ፤ ለምን እንዳልተጠቀማችሁበት መርምራችሁ ልትመልሱ ይገባል” ነው ያሉት።

ሰላምን ለማጽናት ክህደትን ማውገዝ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ በሰሜኑ ጦርነት በነበረው ችግር ሕዝብን ከመከራ ለመጠበቅ መስዋዕት የኾነን መከላከያ ሠራዊት የካዱ ወገኖች ከውስጣችሁ ተፈጥረዋል ብለዋል። እነዚህን ተው ብሎ መመለስ ከራያ ቆቦ ሕዝብ ይጠበቃል ብለዋል።

የማንነት እና የወሰን ጥያቄን ለመመለስ መንግሥት እስከ መጨረሻው ይሠራል። የወሰን እና የማንነት ጥያቄው መልስ የተደናቀፈው በልጆቻችሁ ነውና ልጆቻችሁን መመለስ ላይ ሥሩ ነው ያሉት። “ራያ ጀግና ነው፤ ውብ ባሕል አለው። ባሕሉን ለቱሪስት መስህብ ይጠቀምበት፤ ግጭትን ለማስቀረት ይጠቀምበት፤ ኀላፊነታችሁን እና የሽምግልና አቅማችሁን ካልተወጣችሁ አካባቢው የከፋ ችግር ይገጥመዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የልማት ሥራው ላይ መንግሥት ይሠራል። የሆስፒታል፤ የውኃ እና የመንገድ የመሠረተ ልማት መንግሥት ይፈታል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ጥያቄዎች በፍጥነት እንዲመለሱ ሕዝብ ለሰላም መስፈን መተባበር አለበት” አቶ ፍስሃ ደሳለኝ
Next article“የሰላሙም ኾነ የልማቱ ቁልፍ ያለው በሕዝብ እጅ ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፍዬ