
ወልድያ: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከራያ ቆቦ ወረዳ እና ከቆቦ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በቆቦ ከተማ ምክክር አድርገዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች አንድ በመኾን አካባቢን ማልማት እና ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ ገልጸዋል። ሁሉም ልጆቹን መክሮ ወደ ሰላም መመለስ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የማንነት ጥያቄ ያላቸው የራያ አካባቢዎች አፋጣኝ መልስ ይሰጥ ያሉት ተሳታፊዎቹ የሕወሃት ታጣቂዎች በወረሯቸው የራያ አካባቢዎች ንጹሐን ስቃይ እና እንግልት እየደረሰባቸው መኾኑን አስረድተዋል። የራያ ባሕል ማዕከል ግንባታ መዘግየት እና የአስፓልት መንገድ ማሻሻያ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።
ከተማን ከቀበሌ የሚያገናኙ የጠጠር መንገድ እና የቴሌ ኔትወርክ የማይደርስባቸው፣ የውኃ እጥረት ያለባቸው ቀበሌዎችም ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። የቆቦ ጊራና መስኖ ልማት ያለበት ችግር እንዲፈታም ተሳታፊዎች አንስተዋል። የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች አንዳይፈቱ የሰላሙ ሁኔታ እንቅፋት መኾኑን ተናግረዋል። የተዘጉ ትምህርት ቤቶችም እንዲከፈቱ ሕዝቡ ጥረት እንዲያደርግም አሳስበዋል።
የራሳችን ልጆች ጠበንጃ ታጥቀው ገቢ እንዳይሠበሠብ እየከለከሉ ባለበት ሁኔታ ለልማት የሚኾን በጀት መሰብሰብ አይቻልም ነው ያሉት። ይህን ጉዳይ የቆቦ ከተማ እና የራያ ቆቦ ወረዳ ሕዝብ በደምብ ያውቀዋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በሰላም፣ በድርድር እና በሽምግልና ችግሩ አንዲፈታ የሕዝቡ ጥረቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል።
የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ለመፍትሔው ዕውነቱን መነጋገር ይገባል ነው ያሉት። የጠየቁት ጥያቄም መልስ እንዲያገኝ እንደሚሠሩ ነው ያስገነዘቡት። ሀብት እያለ ራስን ወደ ድህነት መክተት እንደማይገባም አሳስበዋል። ሁሉም ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እና በቅርብ የሚመለሱት ሰላም ሲኖር ብቻ እንደኾነም ተናግረዋል።
የራያ ቆቦ ሕዝብ የሰላምን ችግር በሰሜኑ ጦርነት በሚገባ የሚያውቅ ነው ያሉት ኀላፊው ለችግሮች መልስ ለማግኘት ይቻል ዘንድ ሕዝቡ ስለሰ ሰላም የዕውነት መነጋገር ይኖርበታል ነው ያሉት።
ከማንነት እና ከወሰን ጥያቄ አኳያ ብልጽግና ፓርቲ ጥያቄው መፈታት አለበት በሚል የፓርቲው የኘሮግራም አካል ተደርጓል ብለዋል።በሕዝበ ውሳኔ ጥያቄው መልስ እንዲሰጠው ተወስኖ ወደ ሥራ ሲገባ የክልሉ ሰላም በመደፍረሱ ተደናቅፏል ነው ያሉት።
ጥያቄው በፍጥነት እንዲመለስም ሕዝብ ሰላም በማስፈን ረገድ መተባበር አለበት ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!