ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የምክክር ኮሚሽኑ ወሳኝ መኾኑ ተገለጸ።

17

ባሕር ዳር: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የያዛቸው ግቦች ለሀገራዊ መግባባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የኢትየጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መሪዎች እና አባላት አስታውቀዋል፡፡ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መሠረታዊ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናት እና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሠብሠብ መፍትሄ ለማስቀመጥ ዓላማ ይዞ የተቋቋመ ነው፡፡

ከሕዝብ በተሠበሠቡ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱ የመከታተያ ሥርዓት በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አንዱ ግቡ ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መሪዎች እና አባላት እንደገለጹት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የያዛቸው ግቦች ለሀገራዊ መግባባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንተነህ አዲሱ የምክክር ኮሚሽኑ የያዛቸው አጀንዳዎች ውጤታቸው በሕዝብ ዘንድ የሚናፈቅ ነው ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ የጀመራቸው ተግባራት ወሳኝ በመኾናቸው ለስኬታማነቱ ሁሉም አካል በትኩረት መሥራት አለበት ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል እስማኤል አሊ በበኩላቸው ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የምክክር ኮሚሽኑ ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ሚና ያለው መኾኑን አንስተው ነጻ እና ገለልተኛ በመኾን ለኮሚሽኑ ውጤታማነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቦጋለ ቢተና ሰላም ከሌለ ነጋዴው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ መሥራት እንደማይችል ጠቅሰው ለሀገራዊ መግባባት የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡ የምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት በጎ ነገር ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንግድ ምክር ቤት አባል አበባየሁ ኃይሌ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የኮሚሽኑ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጭዎቹ በመመካከር እና በመወያየት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ተናግረው የምክክር ኮሚሽኑ የጀመራቸው ሥራዎች ችግሮችን በመፍታት ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ኮሚሽኑ የጀመራቸው መልካም ተግባራት ስኬታማ እንዲኾኑ ኀላፊነት በመውሰድ መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ እንደ ኢዜአ ዘገባ ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲኾኑ የንግዱ ማኅበረሰብ ድጋፉን እንደሚያጠናክርም አመላክተዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጸጥታ ችግር ተቋርጦ የነበረው የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ መጀመሩን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next article“ጥያቄዎች በፍጥነት እንዲመለሱ ሕዝብ ለሰላም መስፈን መተባበር አለበት” አቶ ፍስሃ ደሳለኝ