በግብርና ልማቱ የሚያጋጥሙ የግብዓት አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር እና የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የሰሞኑ ጉብኝት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ተናገሩ።

476

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድሩ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ዞኖች ሲያካሂዱ የነበረውን የመስክ ምልከታ አጠናቅቀዋል።

ዛሬ በሰሜን ወሎ ዞን በሀብሩ፣ ጉባላፍቶና ራያ ቆቦ ወረዳዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የመስኖ ልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል። 2 ሺ 800 ሄክታር መሬትን በመስኖ እያለማ ያለው የራያ ቆቦ ሸለቆ ልማትም የጉብኝታቸው አካል ነበር።
አርሶ አደሮች አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቀው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በኩታ ገጠም እርሻ ሙዝ፣ ማንጎና ፓፓያን የመሳሰሉትን በማልማት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑንም አርሶ አደሮቹ ለአብመድ ተናግረዋል። በመስኖ ልማት እንቅስቃሴያቸው የግብዓት አቅርቦትና የጸረ ተባይ ኬሚካል አቅርቦት ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ተስፋሁን ባንታብል እንዳሉት በዚህ ዓመት ብቻ አርሶ አደሩን በመስኖ ተጠቃሚ ለማድረግ 85 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው 41 ፕሮጀክቶች እየተገነቡ።
በዞኑ ከ14ሺ በላይ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋሁን ‘‘አርሶ አደሮች የሚያቀርቡትን የጸረ ተባይና የግብዓት እጥረት ለመፍታት እየሠራን ነው’’ ብለዋል።

በአማራ ክልል በመጀመሪያ ዙር መስኖ 219 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአዝዕርትና አትክልትና ፍራፍሬ መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል። በ2ኛ ዙር መስኖም ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ መለሰ መኮንን (ዶክተር) ተናግረዋል። አርሶ አደሮች የሚያጋጥማቸው የተሻሻሉ ዘሮች እጥረትና ተያያዥ ችግሮች እንዲፈቱላቸው በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው የሰሞኑ ጉብኝት ‘‘ክልሉ በመስኖና በችግኝ ልማት ትልቅ አቅም ያለውና አርሶ አደሮችም በባለሙያ ከታገዙ እስከ ውጭ ገበያ ድረስ መግባት እንደሚችሉ ያሳዬን ነው’’ ብለዋል።

‘‘በግብርና ልማቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመለዬት በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማስቀመጥ በትጋት እንሠራለን፤ ጉብኝቱም ትልቅ አቅም ይፈጥርልናል’’ ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ

Previous articleየተከዜ ዓሳ ሀብትን ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎች ለአራት ወረዳዎች ተሰጡ።
Next articleየኮሮና ወረርሽኝ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ አካል ጉዳተኞችን ሕይወት እየፈተነ ነው፡፡