በጸጥታ ችግር ተቋርጦ የነበረው የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ መጀመሩን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

30

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በጸጥታ ችግር ተቋርጦ የነበረው የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ መጀመሩን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ አስታውቋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል እየሠራ መኾኑንም ገልጿል። ከተማ አሥተዳደሩ በክፍለ ከተሞች ሕጋዊ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለሚፈልጉ ግለሰቦች አገልግሎት እየሰጠ መኾኑም ተነግሯል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ ኀላፊ መኮነን ደባሱ አርሶ አደሮችም ኾኑ ባለይዞታዎች መሬቱን በተቀመጠው አዋጅ እና መመሪያ መሠረት እንዲጠቀሙበት ከደላሎች ነጻ በሆነ መልኩ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታውን በመጠቀም የከተማ መሬትን ሕጋዊ ባልኾነ መንገድ መጠቀም የሚፈልጉ አካላትን ለመከላከል እና ሕግን ለማስከበር ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

በጸጥታ ችግር ተቋርጦ የነበረውን የይዞታ ማረጋገጥ አገልግሎት በማስጀመር ባለይዞታዎች ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እየተሰጣቸው ነው ብለዋል፡፡ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማጥራት እና በማረጋገጥ በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥነት ለመከላከል እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድ እና ለመኖሪያ አካባቢ ልማት እንዲውል ተገቢው ጥናት እየተደረገ ነው ብለዋል። ሕግ እና መመሪያን በጠበቀ መንገድ የካሳ ግምት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። አረሶ አደሮች እና ባለይዞታዎች ከደላሎች ራሳቸውን ነጻ በማድረግ ተገቢውን ሕጋዊ የሰነድ ማረጋገጫ ማግኘት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለነጻነት የፈሰሱ ደሞች፤ ለዕውነት የተከሰከሱ አጥንቶች”
Next articleችግሮችን በውይይት ለመፍታት የምክክር ኮሚሽኑ ወሳኝ መኾኑ ተገለጸ።