
ባሕር ዳር: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግኖች ስለ ነጻነት የጭንቅ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ የማይነጉ የሚመስሉ ሌሊቶችን አንግተዋል፡፡ በእሾህ እና በአሜካላ ተመላልሰዋል፡፡ ከሞት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀዋል፡፡ ሞት ሳያስፈራቸው፣ መከራ ሳያዝላቸው፣ በደል ሳያስቆማቸው ለሀገራቸው ነጻነት መስዋዕት ከፍለዋል፡፡ በመስዋዕትነታቸው ሀገር አጽንተዋል፡፡ ሉዓላዊነትን አስከብረዋል፡፡ የቆዬን ክብር ጠብቀዋል፡፡ ነጻነትን በጽኑ መሠረት ላይ ተክለዋል፡፡
ሳይነኳቸው ነኳቸው፣ ሳይደርሱባቸው ደረሱባቸው፣ ጦር ሳያዘምቱባቸው ጦር አዘመቱባቸው፡፡ ሰይፍ ሳሉባቸው፡፡ በደም እና በአጥንት ማሕተም የተቀበሏትን፣ በከበረች ቃል ኪዳን የጠበቋትን ሀገራቸውን ሊቀሟቸው ተነሱባቸው፡፡ ጀግኖችም ሳይነኳቸው የነኳቸውን፣ ሳይደርሱባቸው የደረሱባቸውን፣ ሀገራቸውን ለመቀማት የመጡባቸውን በጀግንነት መለሷቸው፡፡ የፎከሩትን አሳፈሯቸው፡፡ እንደ ጨው ዘር በተኗቸው፡፡ በተራራ አናት ላይ እንደተበተነ ዱቄት አስመሰሏቸው፡፡
ለቅኝ ግዛት የመጡትን ደመሰሷቸው፡፡ በላኪወቻቸው ፊት አዋረዷቸው፡፡ ከፍ ብለው በኖሩበት የጦር ሜዳ እንዳልነበር አደረጓቸው፡፡ የጀግንነትን ልክ አሳዩዋቸው፡፡ ኢትዮጵያን ለመያዝ የቋመጡት የሮምን ሹማምንት፣ በሹማምንቱ ፊት የፎከሩትን ጎበዛዝት፣ ልጆቻቸውን፣ ባሎቻቸውን እና ወንድሞቻቸውን ሂዱ ብለው ያደፋፈሩትን ወይዛዝርት ሁሉ መና አስቀሯቸው፡፡ በሹማምንቱ ፊት ፎክረው የመጡ የጣሊያን ወራሪዎች የኢትዮጵያውያን ጎራዴ በላቸው፡፡ የድል ብሥራት ለጌቶቻቸው ለማድረስ የቋመጡትን ድባቅ መቷቸው፡፡
ኢትዮጵያን ጠላት ሲነካ እንኳንስ ኢትዮጵያውያን ጋራው እና ሸንተረሩ ይቆጣል፡፡ ሜዳው እና ሸለቆው በግፍ የረገጠውን ጠላቱን ሊበላ ያሰፈስፋል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ጀግኖች ጦርና ጎራዴ እያጋለጠ ይሰጣል፡፡ “ ሀገሬ ኢትዮጵያ ያ ግድም ያ ግድም አንጋዳው ክፉ ነው አያረማምድም” እየተባለ የሚዜምለት የኢትዮጵያ ጎዳና የጣሊያንን ወራሪ አስቀረው፡፡ እንደ ንብ የሚናደፉት ጀገኖች በጀግንነት መክተው፣ ወራሪውን እንዳልነበር አደረጉት፡፡ በዓድዋ አናት ላይ ከዚያም በቀደሙ የወረራ ሙከራዎች ድል የተመታችው ጣሊያን የረከሰባት ስሟን፣ የተሰበረባት ቅስሟን፣ በዓለም አደባባይ የጣለችውን ክብሯን ልታስመልስ፣ ለበቀል ዳግም መጥታ ነበር፡፡ ይህም ዘመን የማይጨው ጦርነት ወይም የኢጣሊያ ወረራ እየተባለ ይጠራል፡፡ በዚህ ዘመን ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ ያልፈጸመችው ግፍ፣ ያላደረሰችው በደል የለም፡፡ ነገር ግን ሁሉንም አድርጋ ተሸንፋ ከመመለስ፣ ተዋርዳ ከመሄድ ያዳናት ማንም አልነበረም፡፡ አያሌ ግፎችን ብትሰራም ድል ከመኾን አልቀረችም፡፡ ኢትዮጵያም እንደተለመደው ድል ከማድረግ ያስቀራት ማንም የለም፡፡
ሀገራችን አናስነካም ያሉ ልባሞች የመርዝ ቦንብ ተጥሎባቸዋል፡፡ በተዘጋ ቤት ውስጥ እሳት ነድዶባቸዋል፣ የተሳለ ሰይፍ በአንገታቸው ላይ አርፎባቸዋል፣ የተሾለ ጦር ተወርውሮባቸዋል፡፡ መርዝ የሚተፋ ጠመንጃ ተነባብሮባቸዋል፡፡ ተድላ ዘዮሐንስ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት ከቅኝ ግዛ ፍላጎት ውጭ ሌላ ምንም ምክንያት አልነበራትም ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የበደለችው በደል የለም፡፡ ጣሊያናውያን በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ ፍጹም ጭካኔ አሳይተዋል፡፡ ልጅ አዋቂ፣ ሴት ሽማግሌ፣ ቄስ መነኩሴ፣ ሳይሉ በመላ የኢትዮጵያውያንን ዘር ከምድረ ገጽ ለማጥፋት፣ ከመሪ እስከ ተራው ሕዝብ ተባብረው በሙሉ ኀይላቸው ተጣጥረዋል፡፡ ለዚህ አንድ ሁለት የለውም፡፡ በዓለም የተከለከለ መርዝ እየረጩ ሰው እና አራዊትን አንድ አድርገው ፈጅተዋል ይላሉ፡፡
በነጻ ሀገር እና በነጻ ሕዝብ ላይ ዘመቻ ያወጁት ጣሊያናውያን ኢትዮጵያውያንን በግፍ ገድለዋል፡፡ አብያተክርስቲያናትን እና ገዳማትን አቃጥለዋል፡፡ ድል ያመጣልናል ብለው ያሰቡትን የግፍ ግፍ ሁሉ ፈጽመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን መከራ እየወረደባቸው፣ የግፍ ዝናብ እየዘነበባቸው፣ የጭካኔ በረዶ እየደበደባቸው እነርሱ ከጽናት መሠረታቸው ንቅንቅ አላሉም፡፡ ስለ ለነጻነት እና ስለ ሉዓላዊነት ሲሉ መከራ ያበረታቸዋል፡፡ ግፍ ያጸናቸዋል እንጂ፡፡
ተድላ ዘዮሐንስ ስለ ጣልያኖች ጭካኔ ሲጽፉ የጣሊያኖች ጭካኔ የሚለካው በፈጁት ሰው ብዛት፣ ባቃጠሉት ቤተክርስቲያን እና ቤቶች ብቻ አይደለም፡፡ ከአገዳደላቸው ጭምር ነው እንጂ ይላሉ፡፡ ቤት እየዘጉ በእሳት ያቃጠሏቸው ብዙ ናቸው፡፡ መርዝ ያርከፈከፉባቸው አያሌ ናቸው፡፡ እጅ ወይም እግራቸውን በሽቦ እያሰሩ በመኪና የጎተቷቸው በርካታ ናቸው፡፡ እጃቸውን ከአንድ መኪና እግራቸውን ከሌላ መኪና ላይ አሥራው መኪናዎቹን ግራና ቀኝ በመንዳት የበጣጠሷቸውም አሉ፡፡ ከእነ ነፍሳቸው የተቀበሩ አሉ፡፡ ወንዶች እንዲሰለቡ፣ ሴቶች ጡታቸውን እንዲቆረጡ አድርገዋልና ነው የሚሉት፡፡ የካቲት 12/1929 ዓ.ም የተፈጸመው ጭካኔ ደግሞ የከፋው ጭካኔ ነበር፡፡ የግፍ አይነቶችን ሁሉ ፈጽመውበታልና ብለዋል፡፡
ኢሜሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢጣሊያ ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12/1929 ዓ.ም ነው ብለዋል፡፡ አብረሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦንብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ ጥቁር ሸሚዝ እየተባሉ የሚታወቁት የፋሽስት ደቀ መዛሙርት በፋሽስቱ አገዛዝ አይዞህ ባይነት አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ደሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከእነ ነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ የተማሩት በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጨፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመኾኑም በሀገሪቱ የፖለቲካ እና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሻር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡
ይህ የፋሺስት ጭፍጨፋ በሌላ መልኩ በወራሪ እና በተወራሪ መካከል ያለው ቅራኔ መካረር በማመልከት የጸረ ኢጣልያ ተቃውሞውም ከመጀመሪያው ወደ ሁለተኛው፣ ከመደበኛ ወደ ከፊል መደበኛ ጦርነት እና ወደ ሽምቅ ውጊያ መሸጋገሩን አረጋገጠ ብለው ጽፈዋል፡፡ ጣልያናውያን በፈጸሙት ግፍ እና ባሳዩት ጭካኔ ኢትዮጵያውያን ፈርተው እና ደንግጠው ዝም ብለው የሚገዟቸው መስሏቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን መከራ እንደሚያበረታቸው፣ በደል እንደሚጸናቸው፣ በሀገራቸው፣ በሠንደቅ ዓላማቸው እና በክብራቸው የትኛውም መከራ ቢመጣ ወደኋላ እንደማይሉ አላወቁም፡፡ ይባስ ብሎ የፈጸሙት በደል እንደ አራስ ነብር አደረጋቸው፡፡ ይባስ ብሎ እንደ ቀትር እሳት አንቀለቀላቸው እና በእልህ፣ በወኔ እና በጽናት እንዲነሱ አደረጋቸው እንጂ፡፡
ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት በተሰኘው መጽሐፋቸው በየካቲት 12 ቀን የጣሊያን ወታደሮች ሽማግሌዎችን፣ ዓይነ ሰውራንን፣ እግር የሌላቸውን ድሆችን፣ እናቶችን ከእነ ልጆቻቸው ሳይቀር እንደጨፈጨፏቸው ጽፈዋል፡፡ የሀንጋሪው ሐኪም ዶክተር ላዲስላስ ላቫ ጠቅሰው ያን የግፍ መዓት ሲጽፉ “ ሱቆች ሁሉ እንዲዘጉ አደረጉ፡፡ የውጭ ሀገር ሰዎችም ከቤታቸው እንዳይወጡ አዘዙ፡፡ በተለይ ፎቶ ግራፍ ማንሻ እየተፈተሸ ይወሰድ ጀመር፡፡ መንገዱ ሁሉ ጭር አለ፡፡ የፖስታ እና የስልክ አገልግሎት ተቋረጠ፡፡ በቤተ መንግሥቱ እና በአካባቢው ያሉ መንገዶች ሁሉ በሬሳ ተሸፈኑ፡፡
ምን አይነት አጨካከን ነው? ደም እንደ ውኃ ሲፈስስ በየመንገዱ ላይ ያየሁት የዚያን ጊዜ ነው፡፡ የወንዶች፣ የሴቶች፣ የልጆች ሬሳ በየአለበት ተኝቷል፡፡ ወዲያውም ከባድ የቃጠሎ ጭስ ተነስቶ ከተማዋን አጨለማት፡፡ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ ቤቱ በእሳት ይቃጠላል፡፡ ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም ቤንዚን እና ዘይት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሰው እሳቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየስ ይገድሉታል፡፡ ሌሊቱንም ሲገድሉ እና ሲያቃጥሉ አደሩ ብለዋል፡፡
ለነጻነት የፈሰሱ ደሞች፣ ለእውነት የተከሰከሱ አጥንቶች በረከቱ፡፡ ቢበዛም ጭንቁ ቢጠንክርም፣ ጽልመቱ ቢሰፋም ኢትዮጵያውያን ግን ለነጻነት በእልህ ተነሱ፡፡ በቁጭት ተሠባሠቡ፡፡ ዱር ቤቴ ብለው ታገሉ፡፡ ጠላትንም በነበልባል ክንዳቸው ቀጥቅጠው ድልን አወጁ፡፡ ነጻነታቸውንም አወጁ፡፡ የጣልያን የመጨረሻው የግፍ ጥግ የታየባት፣ ኢትዮጵያውንም መከራ የተቀበሉባት፣ ግፍንም ያስወግዱ ዘንድ በደም ላይ ቆመው በእልህ የተነሱባት የካቲት 12 ትታሰባለች፡፡ በትውልድ ቅብብሎሽ ትዘከራለች፡፡ ክብር ለነጻነት ለሞቱት፡፡ ለዕውነት ለተሰውት ይሁን፡፡
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!