“የሥራ ዕድል ፈጠራ ከዳቦ ባሻገር ሀገርን የመገንባት ጉዳይ ነው” አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው

27

እንጅባራ: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ምክር ቤት ያለፉትን ሰባት ወራት የሥራ አፈጻጸም በእንጅባራ ከተማ ገምግሟል።

በ2017 በጀት ዓመት ከ71 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት ሰባት ወራት 29 ሺህ 180 ለሚኾኑ ወጣቶች ሥራ መፍጠር ተችሏል። ይህም በበጀት ዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ 41 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ታፈረ ከበደ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 83 በመቶ የሚኾነው ቋሚ የሥራ ዕድል ድርሻ ያለው መኾኑን ተናግረዋል። በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ለ748 ሴት ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ኀላፊው አንስተዋል። የሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ወጣቶች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የመሥሪያ ብድር ተመቻችቶላቸዋል ነው ያሉት።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው “የሥራ ዕድል ፈጠራ ከዳቦ ባሻገር ሀገርን የመገንባት ጉዳይ መኾኑን” ተናግረዋል። ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያግዙ በርካታ ጸጋዎች እንዳሉት ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው ሁሉንም ጸጋዎች አሟጦ በመጠቀም ወጣቶችን ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሁሉንም የተመዘገቡ ወጣቶችን በወቅቱ ወደ ሥራ ማስገባት፤ የተሰራጨ ብድር በአግባቡ መሰብሰብ ፣ የመሸጫ እና የመሥሪያ ቦታ ግንባታን ማፋጠን እና የሰላም ሁኔታ መሻሻል የታየባቸውን ወረዳዎች በተሟላ መልኩ ወደ ሥራ ማስገባት ቀጣይ በትኩረት መፈጸም የሚገባቸው ጉዳዮች እንደኾኑም ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የክብር ኒሻን ተሸለሙ።
Next article“ለነጻነት የፈሰሱ ደሞች፤ ለዕውነት የተከሰከሱ አጥንቶች”