የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የክብር ኒሻን ተሸለሙ።

51

ባሕርዳር: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ ዕድገት ላበረከቱት የጎላ አስተዋጽኦ በሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የክብር ኒሻን ተሸልመዋል፡፡ ሽልማቱን ያበረከቱት የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀመንበር ሚስዝ ቫለቲና ማትቬንኮ ይህ የክብር ኒሻን ለምክር ቤቶች ፓርላሜንታዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለሩሲያና ለውጭ ሀገራት ዜጎች እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ይህ ታላቅ የክብር ኒሻን ለመሸለም በሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቻምበር ሲወሰን ብቻ እንደኾነም አንስተዋል። አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለዚህ የእውቅና ሽልማት በመብቃትዎ እንኳን ደስ ያለዎት ብለዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለተሰጣቸው የእውቅና ሽልማት የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤትን አመሰግነዋል። ይህ ኒሻን ለፌዴሬሽን ፓርላሜንታዊ ዕድገት የበለጠ እንዲሠሩ የሚያበረታታ መኾኑን ገልጸዋል ፡፡

የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የክብር ኒሻን የሚሸልመው ለዜጎች ነፃነትና ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ለታገሉ፣ ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጠናከር ከፍተኛ ድርሻ ላላቸው፣ በምክር ቤቶች መካከል የሚኖረው ግንኙነት የላቀ እምርታ እንዲያሳይ እና የጋራ መግባባት እንዲፈጠር የጎላ አበርክቶ ለሰጡ ግለሰቦች ነው፡፡

ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ይህ የክብር ኒሻን ሽልማት ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት መከተል ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ለኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሲሰጥ የመጀመሪያው እንደኾነ ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
Next article“የሥራ ዕድል ፈጠራ ከዳቦ ባሻገር ሀገርን የመገንባት ጉዳይ ነው” አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው